የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ አዲስ የአመራር ቢሮ አዋቀረ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ አዲስ የአመራር ቢሮ አዋቀረ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ በአህጉሪቷ የፖለቲካ ትብብርን ለማጠናከር እና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለማጎልበት ያለመ አዲስ የቢሮ አመራር አዋቅሯል።
በአዲስ አበባ በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ማጠቃለያ ይፋ የተደረገው አዲሱ አመራር ከመላው አፍሪካ የተወጣጡ ታዋቂ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና የተቋማት ተወካዮችን ያካተተ ነው።
በዚህም የጋና ብሔራዊ ዴሞክራቲክ ኮንግረስ ብሔራዊ ሊቀ መንበር ጆንሰን አስይዴህ ንኬቲያ የቢሮው ሊቀ መንበር ሆነው ተመርጠዋል።
ከኢትዮጵያ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ የኢኒሼቲቩ ዋና ጸሐፊ ሆነው ተሰይመዋል።
የኢኒኜቲቩ ሊቀ መንበር ጆንሰን አስይዴህ ንኬቲያ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አፍሪካ ያላትን የሕዝብ ቁጥር እና የተፈጥሮ ሀብት አቅም ወደ ተጨባጭ ምርታማነት፣ ብልፅግና እና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ለመቀየር ብቁ የፖለቲካ ተቋማት፣ ጠንካራ የፖሊሲ አቅም እና የረጅም ጊዜ አመራር ያስፈልጋታል።
የፖለቲካ ፓርቲ የምርጫ ውድድርን ለማሸነፍ ብቻ የሚደራጅ ሳይሆን የወደፊት መንግሥት የሚቀረጽበት ዋነኛ ተቋም መሆኑን ገልጸው፤ ፓርቲዎች በምርጫ ማሸነፍ ላይ ብቻ ሳያተኩሩ በውጤታማነት ለመምራት የሚያስችል እውቀት፣ ተቋማዊ አቅም እና አመራር ሊገነቡ ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ ህዝብ ቁጥር በየጊዜው እያሻቀበ መምጣቱን ያስታወሱት የኢኒሼቲቩ ሊቀ መንበር፤ የተፈጥሮ ሀብትን ለኢንዱስትሪ ልማት በማዋል፣ ግብርና በማቀነባበር፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራን በማዳበር ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ 2040 የፖለቲካ ተቋማትን ለማጠናከር፣ የአመራር አቅምን ለማሳደግ እና የቀጣዮችን የአፍሪካ የፖለቲካ መሪዎች ለማዘጋጀት የሚያስችል የጋራ ማዕቀፍ መሆን አለበት ብለዋል።
የኢኒሼቲቩን አህጉራዊ ወካይነት ለማረጋገጥ ከአምስቱም የአፍሪካ ክልሎች ምክትል ሊቀ መናብርት መሰየማቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ለሰሜን አፍሪካ ከአልጄሪያ ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር አብደልከሪም ቤንምባሬክ እና ከሞሪታኒያ የዕድገት ኃይሎች ኅብረት መሐመድ ኦልድ ሙሉድ ተወክለዋል።
ለምዕራብ አፍሪካ ከላይቤሪያ ዩኒቲ ፓርቲ ዶክተር ሉተር ታርፔህ እና ከአይቮሪኮስት ኢቮሪያን ፖፑላር ግንባር ፓስካል አፊ ንጌሳን ተሰይመዋል።
ለማዕከላዊ አፍሪካ ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የዴሞክራሲና ማኅበራዊ ዕድገት ኅብረት ኦጉስቲን ካቡያ እና ከካሜሩን ሶሻል ዴሞክራቲክ ፍሮንት ጆሹዋ ኦሲህ ተካተዋል።
ምሥራቅ አፍሪካ ከታንዛኒያ ቻማ ቻ ማፒንዱዚ ዶክተር አሻ-ሮዝ ሚጊሮ እና ከኡጋንዳ ብሔራዊ ሪዚስታንስ ንቅናቄ ሪቻርድ ቶድዎንግ ተወክለዋል።
ለደቡባዊ አፍሪካ ከሌሶቶ ለብልፅግና አብዮት ፓርቲ ንታቲ ሞሮሲ እና ከናሚቢያ ስዋፖ ፓርቲ ሶፊያ ሻኒንግዋ በተመሳሳይ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
በተቋማዊ አመራር ዘርፍ የአፍሪካ አስተዳደር ማዕከል ተወካይ ቤኔዲክት ላሲ የተቋማዊ ጉዳዮች ተባባሪ ሊቀ መንበር ሆነው ሲሾሙ፣ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ኔልሰን ኦፖንግ በአመራር አካሉ ውስጥ ተካተዋል።
የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ተወካይ ፕሮፌሰር ሞዴስት ባሃቲ ሉክዌቦ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትምህርትና ልማት ክፍልን እንዲመሩ ተመድበዋል።