ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለአፍሪካ የልማትና ኢኮኖሚ ሽግግር የሚሰጡት ትኩረት የሚያስደንቅ ነው - የፓን አፍሪካ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ፋቲህ ቡትቢግ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለአፍሪካ ልማትና ለኢኮኖሚያዊ ሽግግር የሚሰጡት ትኩረት የሚያስደንቅ መሆኑን የፓን አፍሪካ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋቲህ ቡትቢግ ገለጹ። 

ፕሬዝዳንቱ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ጉባዔውን በብቃት ላስተናገደው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

ጉባዔው በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄዱ ትልቅ ታሪካዊ ትርጉም እንዳለው ጠቁመው፤ ዓድዋ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ላይ የተቀዳጁትን ታላቅ የነፃነት ድል የሚያስታውስ  መሆኑን ተናግረዋል። 

ይህም ልክ እንደነጻነት ትግሉ የወቅቱን ለኢኮኖሚ ነፃነት የሚደረገውን ትግል የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

አፍሪካ ከቀደሙት አባቶች የተቀበለችውን የፖለቲካ ነፃነት ወደ ኢኮኖሚ ነፃነት፣ ተቋማዊ ጥንካሬ እና ሉዓላዊ አህጉራዊ ዕድገት ማሸጋገር እንደሚገባትም አሳስበዋል።

የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ውድድር ላይ ብቻ ከማተኮር ተሻግረው ተቋማዊ አቅምን ለመገንባት፣ ፖሊሲዎችን ለማውጣት እና አህጉራዊውን ኢኮኖሚ ለመቀየር የቀዳሚነት ሚና መጫወት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የፓን አፍሪካ ፓርላማ ከአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሌሎች አህጉራዊ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ከሕዝብ አስተዳደር ማዕከል ጋር በመተባበር በ2027 የእርስ በእርስ ግጭትን መከላከል፣ ሰላምና መልካም አስተዳደርን ማስፈን ላይ ያተኮረ አህጉራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ እንደሚያዘጋጅ አስታውቀዋል።

በመጪው ታህሳስ የአፍሪካ የሕግ አውጪ ጥናትና ምርምር ማዕከል በይፋ እንደሚመሠረት፣ በሚቀጥለው ዓመት የመጀመሪያው የአፍሪካ ፓርላማ ዩኒቨርሲቲ እንደሚከፈት እንዲሁም የአፍሪካ ሴቶች እና ወጣቶች ፓርላሜንታሪያን አህጉራዊ ጉባዔዎች እንደሚካሄዱ ይፋ አድርገዋል። 

አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷን በመጠቀም፣ የኢንዱስትሪ ልማቷን በማፋጠን፣ የነፃ ንግድ ቀጣና  ስምምነትን በመተግበር እና በወጣቶችና ሴቶች ላይ በመዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የአጀንዳ 2063 ግቦችን ማሳካት እንዳለባትም አሳስበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም