በክልሉ የማዕድን ሃብትን በተሻለ መልኩ ለማልማት በሚደረገው ጥረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የማዕድን ሃብትን በተሻለ መልኩ ለማልማት በሚደረገው ጥረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው
ባህር ዳር፤ ጥቅምት 28/2019(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የማዕድን ሃብትን በጥናትና ምርምር በመታገዝ በተሻለ መልኩ ለማልማት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትብብርና እገዛ ወሳኝ መሆኑን የክልሉ የማዕድን ቢሮ ሃላፊ ሐይሌ አበበ ገለጹ።
የአማራ ክልል የማዕድን ቢሮ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሥነ-ምድር ጥናትና የካርታ ሥራ እንዲሁም የማዕድን ፋለጋና ክምችት ግምታዊ ጥናት ላይ በትብብር ለመስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርጓል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የክልሉ የማዕድን ቢሮ ሃላፊ ሐይሌ አበበ፤ የማእድን ዘርፍ ከመሰረታዊ የልማትና እድገት ምሰሶዎች መካከል አንዱ ሆኖ እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በአማራ ክልል ያለውን እምቅ የማእድን ሃብት በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ወሳኝ ድርሻ ያላቸው መሆኑን ጠቁመው በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።
በክልሉ የማዕድን ሃብትን በተሻለ መልኩ ለማልማት በሚደረገው ጥረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን አንስተው በጥናትና ምርምር የሚያደርጉት እገዛ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
የማዕድን ሀብትን በእውቀትና በቴክኖሎጂ ታግዞ ማልማት ከተቻለ በዘርፉ የላቀ ስኬት ማስመዝገብ የሚቻል መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት በክልሉ 2 ሺህ ኪሎ ግራም ወርቅ ለማምረት ታቅዶ በሩብ ዓመቱ 431 ኪሎ ግራም ማምረት መቻሉን ጠቅሰው እቅዱን ለማሳካት ጥረት የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲዎቹ ተወካዮችም የዘርፉን ልማት በጥናትና ምርምር በማገዝ ለተሻለ ስኬት አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ላይ የወሎ፣ የባህር ዳር፣ የጎንደር፣ የእንጅባራ፣ የወልዲያ፣ የደብረብርሃን እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ተገኝተዋል።