ሲዳማ ቡና በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን አስመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
ሲዳማ ቡና በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን አስመዘገበ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሲዳማ ቡና ይርጋጨፌ ቡናን 2 ለ 1 አሸንፏል።
በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ በተካሄደው ጨዋታ መስከረም መኮንን በስድስተኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ጎል ይርጋጨፌ ቡና መሪ ሆኗል።
ቢታኒያ አስተረፍ በ78ኛው በፍጹም ቅጣት ምት እና ምንትዋብ ዮሐንስ በ91ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ባሳረፏቸው ጎሎች ሲዳማ ቡና ድል ተቀዳጅቷል።
በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን ያስመዘገበው ሲዳማ ቡና በሶስት ነጥብ ደረጃውን ከ14ኛ ወደ 7ኛ ከፍ በማድረግ ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል።
በሊጉ ሁለተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ይርጋጨፌ ቡና በአንድ ነጥብ ከነበረበት 12ኛ ደረጃ ወደ 13ኛ ዝቅ በማለት ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።