የኢትዮጵያን የእስልምና ታሪክና መንፈሳዊ እሴቶች ለሀገረ መንግሥትና ለሥልጣኔ ግንባታ ማዋል ያስፈልጋል -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የእስልምና ታሪክና መንፈሳዊ እሴቶች ለሀገረ መንግሥትና ለሥልጣኔ ግንባታ ማዋል ያስፈልጋል -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የእስልምና ታሪክና መንፈሳዊ እሴቶች ለሀገረ መንግሥትና ለሥልጣኔ ግንባታ ማዋል ያስፈልጋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ዛሬ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባዔ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ በመገኘቴ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል።
የነቢዩ ዩሱፍ ታሪክ በቅዱስ ቁርዐን ከሚገኙ ታላላቅ ትምህርቶች አንዱ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የቤተሰብ ፍቅርንና ክህደትን፣ መከራንና ፈተናን፣ በመጨረሻም በእምነትና በፅናት እውነትን ማሸነፍን ያስተምረናል ብለዋል።
ኢትዮጵያም በታሪኳ ብዙ ሤራዎችንና መከዳቶችን አልፋለች ሲሉ ገልጽዋል።
የተተበተቡባትን ወጥመዶች ሁሉ በጣጥሳ ወደ ተገባት ክብርና ሥልጣኔ እንደምትመለስ ያለን እምነት ጽኑ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ልዩ ቦታ ያላት ሀገር ናት ሲሉም ገልጸዋል።
የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) አሳዳጊ የኡም አይመን፣ የመጀመሪያው ሙአዚን ቢላል፣ የመጀመሪያው ሂጅራ እና የነጃሺ ምድር ናት።
አራተኛዋ የሙስሊሞች ቅዱስ ከተማ ተብላ የምትጠራው ሐረር መገኛም ናት። ይህንን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርስ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ ለቱሪዝምና ለዓለም አቀፍ ግንኙነታችን በሚገባ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
የመደመር መንግሥት መንፈሳዊነትን እንደ ታላቅ ሀገራዊ ኃይል ይመለከተዋል ሲሉም ገልጸዋል።
ይህንን ኃይል በአግባቡ ከተጠቀምንበት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት እንችላለን። መንግሥትም የሃይማኖት ተቋማት ጠንካራና ብቁ እንዲሆኑ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።
እኛ ለሀገራችን ያልሠራነውን ማንም አይሠራልንም፤ እኛ ያላሳደግናትን ማንም አያሳድግልንም፤ እኛ ሰላሟን ያልጠበቅንላትን ሀገር ማንም አይጠብቅልንም ሲሉም አስረድተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልእክት “ለሕዝብ እጅግ የሚጠቅሙ ሰዎች፣ እነርሱ በአላህ ዘንድ እጅግ የተወደዱ ናቸው” እንደተባለው የሕዝባችንን ኑሮ፣ ጤና፣ ትምህርትና ሰላም የሚያሻሽል፤ የኢትዮጵያን የመደመር ሥልጣኔ የሚገነባ በጎ ሥራ ሠርተን እንድናልፍ አደራ እላለሁ ብለዋል።