ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን የጤና መድህን አገልግሎት ለዜጎች የሕክምና ተደራሽነት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

ጅማ ፣ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ) ፡-በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን የጤና መድህን አገልግሎት ለዜጎች የሕክምና ተደራሽነት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የዞኑ ጤና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

በዞኑ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የማኅበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት አፈጻጸም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በጅማ ከተማ ተካሂዷል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን የጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፉአድ ሳቢት፣ በዞኑ የጤና አገልግሎትን በማስፋት የዜጎችን የህክምና ፍላጎት ለመሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በዞኑ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የጤና መድን አባል መሆናቸውን አስታውሰው ዘንድሮም ከ1 ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ ሰዎችን የጤና መድን አባል ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ መሐመድ ጣሃ አባ ፊጣ፤ የጤና መድህን አገልግሎትን በማስፋት ለዜጎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የጤና ተቋማትን ግብአት የማሟላት እንዲሁም የህክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በፓርቲው የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዲዳ ጉዳታ በበኩላቸው፣ የመደመር መንግስት የዜጎች ጤና ተጠብቆ አምራችና ውጤታማ መሆን እንዲችሉ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የጤና መድን አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም