2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ የአዲስ አበባ ድንጋጌን በማውጣት ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ የአዲስ አበባ ድንጋጌን በማውጣት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ):- ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ 2040"ን ለማዘጋጀት ቃል የገቡበትን የአዲስ አበባ ድንጋጌ በማውጣት ተጠናቋል።
የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ 2040 የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት የሚያደርጉትን ዘላቂ አስተዋጽኦ ማስቀጠል የሚያስችል ነው።
የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ከጥቅምት 26 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ "ዕድገትን መምራት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሃሳብ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል።
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፓርቲያቸው ብልጽግና አፍሪካውያን በጋራ አጀንዳዎቻቸው ላይ በጋራ እንዲመክሩ ለወሰዱት ተነሳሽነት ምስጋና ተችሯቸዋል።
የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ 2040 ከአፍሪካ ህብረት የዲሞክራሲ፣ ምርጫ እና አስተዳደር ቻርተር፣ ከአጀንዳ 2063፣ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እና ሌሎች ስምምነቶች ጋር የተጣጣመ መሆኑ ተገልጿል።
በጋና በተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ የጸደቀው "የአክራ ድንጋጌ" ለአፍሪካ ሀገራት ሉዓላዊነት፣ ነፃነትና የግዛት አንድነት የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አቋም መያዙ ይታወቃል።
የዘንድሮው በፖለቲካ ፓርቲዎችና በአፍሪካ ኢኮኖሚ ሽግግር ላይ የወጣው "የአዲስ አበባ ድንጋጌ" የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭን አጽድቋል።
በአዲስ አበባ ድንጋጌ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕገ መንግሥታዊ አስተዳደር፣ ውጤታማ የሕዝብ ተቋማትን ለመፍጠር፣ ለፖለቲካ መረጋጋት እና ለአፍሪካ ሕዝቦች የረጅም ጊዜ ብልጽግና ገንቢ ሚና ለመወጣት ቃል ገብተዋል።
ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚለካና በሚተገበር፣ የህዝብን ተጠያቂነት በሚያሰፍን እንዲሁም ተዓማኒነትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ ሰጥተው ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ብሔራዊ የልማት ዕቅዶቻቸውን በማጠናከር ኢንቨስትመንትን ለማስፋትና ውጤታማ የህዝብ ተቋማት እንደሚፈጠሩ በድንጋጌው ተገልጿል።
የኢንዱስትሪ አብዮትን ለማቀጣጠል፣ የኢኮኖሚ ሽግግር ለመፍጠርና የቴክኖሎጂ ልማትን ለማጠናከር የሚያስችሉ የፖለቲካ ፕሮግራሞችን ለመከተል ቃል ገብተዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ዓላማዎች በማሳካት አህጉራዊ ውህደት ለመፍጠር ቃል ኪዳናቸውን አድሰዋል።
የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ 2040 የሚፈለገውን አህጉራዊ ሽግግር ማሳካት እንዲችል ወደ ተግባር እርምጃ እንደሚገቡ አረጋግጠዋል።
በዚህም የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭን በዋና ጸሐፊነት እንዲመሩ የተሾሙት የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) የኢኒሼቲቩ ቢሮ ሴክሬታሪያት ስብሰባዎችን በማድረግ በድንጋጌው የሰፈሩ ቃል ኪዳኖች ገቢራዊ መደረጋቸውን እንዲከታተል ኃላፊነት ተሰጥቶታል።