ጉባዔው የአፍሪካን እምቅ አቅም ወደ ብልፅግና እና ታማኝነት ለመቀየር ያለውን አህጉራዊ የጋራ ኃላፊነት ያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጉባዔው የአፍሪካን እምቅ አቅም ወደ ብልፅግና እና ታማኝነት ለመቀየር ያለውን አህጉራዊ የጋራ ኃላፊነት ያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፦ ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ የአፍሪካን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ዕድል፣ ብልፅግና እና ታማኝነት ለመቀየር ያለውን አህጉራዊ የጋራ ኃላፊነት ያረጋገጠ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
«ዕድገትን መምራት፦ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች» በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ተጠናቋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር ፣ ከመላው አፍሪካ የተወጣጡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ የተቋማት ተወካዮችና እንግዶች አዲስ አበባን የምክክር፣ የእርስ በእርስ ትምህርት እና የአህጉራዊ ዓላማ ማደሻ ስፍራ ስላደረጓት ምስጋና አቅርበዋል።
በጉባዔው ወቅት የተካሄዱትን የስኬታማ ሴቶች እና ወጣቶች መድረኮች እንዲሁም አህጉራዊ ውይይቶችን መካሄዳቸውንም ተናግረዋል።
መድረኩ የአፍሪካን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ዕድል፣ ብልፅግና እና ታማኝነት ለመቀየር ያለውን የጋራ ኃላፊነት ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ በይፋ የጸደቀው «የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን» ለጋራ ውይይቶች ግልጽ አቅጣጫ ያስቀመጠ መሆኑን ጠቁመው፤ የተቀመጡትን ቃል ኪዳኖች ወደ ተግባር ለመቀየር፣ ልምዶችን ለመለዋወጥ እና የተደረጉ ጥረቶችን በሚቀጥለው አህጉራዊ ጉባዔ ላይ ለመገምገም የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱን አስረድተዋል።
አሁን ያለው ዋና ኃላፊነት እነዚህን ውሳኔዎች ወደ ተጨባጭ ተግባር መለወጥ እንደሆነም ገልጸዋል።
በብልፅግና ፓርቲ ስም ለአዲሱ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ (APPI) አመራሮች እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት ብልፅግና ፓርቲ በኢኒሼቲቩ ውስጥ በሚኖረው የዋና ጸሐፊነት ሚና አካታች ትብብርን ለማጠናከር፣ ከሁሉም አባል ፓርቲዎች ጋር በትጋት ለመሥራት እና የጉባዔውን ውሳኔዎች ወደ ተግባር ለመለወጥ ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።