የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት ስላለው በዲፕሎማሲ የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል -ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት ስላለው በዲፕሎማሲ የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል -ምሁራን
ሠመራ፣ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በታሪክ፣ በመልክዓ ምድርና በዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት ስላለው በዲፕሎማሲ የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል ሲሉ የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በታሪክ፣ በመልክዓ ምድርና በዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት ያለውና የማያሻማ ጉዳይ ነው።
ይህ ጥያቄ አሁን ላይ እየገፋና የዚህ ዘመን ትውልድ ጥያቄ ወደ መሆን ደረጃ ደርሷል።
የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ እውን ሆኖ ምላሽ እንዲያገኝ የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እየተካሄዱ ሲሆን፣ የሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲተገበርም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
ይህንን አስመልክተው ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በታሪክ፣ በመልክዓ ምድርና በዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ በየትኛውም መመዘኛ ተገቢና ትክክለኛ ጥያቄ በመሆኑ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ሲሉም ምሁራኑ አክለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የውሃ ሀብትና መስኖ ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የመስክና ቤተ ሙከራ አስተዳደር ዳይሬክተር አብዱልወሀብ አቤ፣ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ይዘትን የተላበሰ መብት መሆኑን ጠቅሰው፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተጀመረው ጥረት የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር መሐመድ አህመድ ኢትዮጵያ በሴራ ባጣችው የባህር በር የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና ልትቀጥል አይገባም ብለዋል።
የባህር በር የማግኘት ጉዳይ የትውልዱ ጥያቄ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ የሚደነቅና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባውም አመልክተዋል።