የመደመር መንግሥት ዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ውጤታማ ተግባር እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት ዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ውጤታማ ተግባር እያከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት ዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ውጤታማ ተግባር እያከናወነ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።
2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሐንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 26 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በመካሄድ ላይ ነው።
በጉባዔው መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ፤ "የአፍሪካ ምርጫዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በሐሰተኛ መረጃ ዘመን" በሚል ርዕስ ቀጥሎ በተካሄደው የዛሬው የፓናል ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እመርታ በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ፤ የመደመር መንግሥት የዲጂታል ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ለአምስት ዓመታት በተተገበረው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለዲጂታል ኢኮኖሚ መሰረት የሚሆኑ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን በጋራ ተሰልፈው ያሳኩት ዳግም ዓድዋ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራት የኃይል ትስስር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የቴሌኮም መሰረተ ልማት ተደራሽነትንና የኢንተርኔት ሽፋንን ማሳደግ መቻሉንና የሞባይል ተጠቃሚዎችም ቁጥርም ማደጉንም ተናግረዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መሰረት ዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በብሔራዊ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለበርካታ ዜጎች ተደራሽ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የዲጂታል ክህሎትን ለማሳደግ የሚያስችል የሥልጠና መርሃ ግብር እየተተገበረ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት በዘርፉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የመደመር የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ለአህጉሪቷ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ክህሎት ግንባታ ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል አንስተዋል።
በመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ በርካታ አገልግሎቶች ዲጂታል መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ በታላቁ ስትራቴጂ መሰረት 95 በመቶ የሚሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአውቶሜሽን ለዜጎች ለማድረስ ግብ መቀመጡን አስታውቀዋል።