በጋምቤላ ክልል የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚጠበቅብንን ግብር በመክፈል ኀላፊነታችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚጠበቅብንን ግብር በመክፈል ኀላፊነታችንን እንወጣለን
ጋምቤላ፣ ጥቅምት 28 / 2019 (ኢዜአ)፡- በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚጠበቅብንን ግብር በመክፈል ኀላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉ በጋምቤላ ክልል ግብር ከፋዮች ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገርናቸው ግብር ከፋይ አቶ ተማም አያሌው፤ የግብር መክፈል ጉዳይ የቀጣዩ ትውልድ መሰረት የሚገነባበት የሀገር አደራና ሃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የሚጠበቅብንን ግብር በወቅቱና በአግባቡ በመክፈል ሃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል።
ግብራቸውን በወቅቱ መክፈላቸውን አስታውሰው ሌሎችም ለግብር ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በጋምቤላ ክልል የተጀመሩ የልማት ስራዎች ትልቅ ተስፋ የተሰነቀባቸው መሆኑን ያነሱት አቶ ተማም፤ የክልሉ ግብር ከፋዮች ለልማት ሃላፊነታችንን መወጣት አለብን ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላኛው ግብር ከፋይ አቶ ቴወድሮስ መኮንን፤ የሀገር እድገት ሊሳካ የሚችለው ከዜጎች በሚሰበሰብ ግብር መሆኑን አንስተው ግብራችንን በወቅቱ በመክፈል ለክልላችን ልማት አጋርነታችንን ማሳየት አለብን ብለዋል።
በክልሉ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት እመርታ እየታየባቸው መሆኑን አንስተው ግብር በመክፈል አጋዥነታችንን በተግባር እናሳያለን ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም በክልላችን የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚጠበቅብንን ግብር በመክፈል አደራችንን እንወጣለን ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቸንኳት ደቪድ፤ በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ በተለይም ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ግብር በታማኝነት መክፈል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የክልሉን የገቢ አቅምን በማሳደግ የታቀዱ የልማት ግቦችን ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ በዘንድሮው በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ11 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ሃላፊው እቅዱን ለማሳካት የባለድርሻ አካላትና የግብር ከፋዮች የጋራ ጥረት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማጠናከር በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ የታቀደውን ግብ ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በክልሉ ሶስት ዞኖችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስተሳሰርና የገቢ ማዕከላትን በማስፋት የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት የልማት እቅዶች የሚሳኩት በግብር ከፋዮች እገዛ በመሆኑ ግብር ከፋዮች በታማኝነት የሚጠበቅባቸውን አደራና ሃላፊነት እንዲወጡ አስገንዝበዋል።