በሴራና በተንኮል የባህር በር እንድናጣና የባህር ኃይላችን እንዲፈርስ መደረጉ ሀገራችንን ለተለያዩ ተግዳሮቶች ዳርጓታል - ኢዜአ አማርኛ
በሴራና በተንኮል የባህር በር እንድናጣና የባህር ኃይላችን እንዲፈርስ መደረጉ ሀገራችንን ለተለያዩ ተግዳሮቶች ዳርጓታል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ) ፦ በሴራና በተንኮል የባህር ኃይላችን እንዲፈርስ ብሎም የባህር በር እንድናጣ መደረጉም ሀገራችንን ለተለያዩ ተግዳሮቶች ዳርጓታል ሲሉ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ገለጹ፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሠራዊት ማህበራት ህብረት አራተኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ከፍተኛ አመራሮች፣ የባህር ኃይል አመራሮች፣ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዋና አዛዡ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ሌላ ሀገርን ለመውረር ያለመ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሕግና በዲፕሎማሲ አማካኝነት መፍትሄ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ነው ፡፡
ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ የተወሰደባትን የባህር በር ለማስመለስ ዝግጁ ናት ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር መራቋ ከሀገሪቱ ታሪካዊ ስብራቶች አንዱ መሆኑን የገለጹት ቫይስ አድሚራል ክንዱ በሴራና በተንኮል የባህር ኃይላችን እንዲፈርስ ብሎም የባህር በር እንድናጣ መደረጉም ሀገራችንን ለተለያዩ ችግሮች ዳርጓታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ታሪካዊ ትስስር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብቻ የተጀመረ እንዳልሆነ አንስተው፣ ሀገራችን አሰብና ምጽዋን ጨምሮ ከቀይ ባህር ጋር የነበራት ታሪካዊ የንግድ ግንኙነት ከጥንታዊ ሥልጣኔ ዘመን ጀምሮ የሚዘልቅ መሆኑን አብራርተዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሠራዊት አባላት በህይወት ዘመናቸው በውትድርና አገልግሎታቸው ያካበቱት ልምድና ያሳረፉት ታሪካዊ አሻራ ለአሁኑና ለቀጣዩ ትውልድ ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
ይህ ልምድና የሀገር ፍቅር መንፈስ ለአሁኑ የባህር ኃይል ግንባታና ለቀጣዩ ትውልድ አርዓያ እንደሚሆን መግለጻቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ መረጃ ያመለክታል።