በክልሉ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል
ሀዋሳ: ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ) :- በሲዳማ ክልል የእንስሳት ዝርያን በማሻሻልና ምርታማነትን በማሳደግ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የሀዋሳ ዳልጋ ከብት አባላዘር ማምረቻ፣ ማቀነባበሪያና ማሰራጫ ማዕከል ገለጸ።
የማዕከሉ የዝርያ ግብአት ምርትና ስርጭት ቡድን መሪ ዶክተር ገዛኸኝ ሽርመካ ማእከሉ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ከእንስሳት ሃብት የሚፈለገውን ጥቅም ለማግኘት ዘመናዊ እርባታን ከመከተል ባለፈ የዝርያ ማሻሻል ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በማዕከሉ አሁን ላይ ምርታማነታቸው የተረጋገጠ የሆላንድ ዝርያ ያላቸው “ሆሊስትን ፊሪዚያ” የተሰኙ የወተት ላም ዝርያዎች በማራባት ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻልና ምርታማነትን በማሳደግ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እየተቻለ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የማዕከሉ ስራ አስኬያጅ አቶ ተመስገን ሙሴ በበኩላቸው የውጭና ሀገር ውስጥ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ኮርማዎች በማምጣት ዘር በማምረትና በማቀነባበር ለአምራቹ የማስራጨት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በእንስሳት ልማት ከቁጥር ይልቅ ጥራትና ምርታማነት ወሳኝ መሆኑን አንስተው የዝርያ ማሻሻልና ምርታማነትን የማሳደግ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።