ቀጥታ፡

የሕግ ታራሚዎች በበጎ ሥነ-ምግባር ታንጸው ለሀገር ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ የማረም ማነጽ የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቷል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ):-የሕግ ታራሚዎች በበጎ ሥነ ምግባር ታንጸው ለሀገር ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ውጤታማ የማረም ማነጽ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ገለጸ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ 

አሌልቱ ከተማ የሚገኘው የፌዴራል ማረሚያ ማሠልጠኛ ተቋም የ13ኛ ዙር የዕጩ መኮንኖች የምረቃና የ38ኛ ዙር ምልምል ኮንስታብሎች የመለዮ ማልበስ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል። 


 

በሥነ ሥርዓቱም የፌዴራል ማረሚያ ማሠልጠኛ ተቋም ወደ ኮሌጅ ማደጉ የተበሰረ ሲሆን፤ በዕለቱም 318 ዕጩ መኮንኖች በረዳት ኢንስፔክተርነት፤ 751 በምልምል ኮንስታብልነት ለምረቃ በቅተዋል።

ተመራቂዎቹም በሥልጠና ቆይታቸው፤ ፖሊሳዊ ሥነ ምግባርና ወታደራዊ ሥልጠናዎችን፣ የአካል ብቃትና የአደጋ መከላከል፣ የወንጀል ሕግና ሥነ ሥርዓት ሙያዊ ክህሎት መቅሰማቸው ተመልክቷል። 

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽነር ጀነራል የኑስ ሙሉ በዚሁ ወቅት፤ በማረም ማነጽ ተግባር የሕግ ታራሚያን ሀገር ገንቢ ሆነው እንዲወጡ እየተደረገ ነው ብለዋል። 

ዘመናዊ የማረሚያ ሥነ ሥርዓት ዋና አቅጣጫ ቅጣትን ማስፈጸም ብቻ ሳይሆን ታራሚያን አምራችና በጎ አስተሳሰብ ተላብሰው እንዲወጡ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚህም የማረሚያ ተቋማትን የማረም ማነጽ ውጤታማነት በማሳደግ በርካታ የለውጥ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። 

ለአብነትም ከ2017 እስከ 2022 ዓ.ም የሚተገበር ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማውጣት የማረሚያ ሥራን በማዘመን በተጨባጭ የሚመዘን አፈጻጸም ሥርዓት እየተገነባ መሆኑን አንስተዋል። 


 

ተመራቂ ዕጩ መኮንኖችና ምልምል ኮንስታብሎችም ተቋማዊ የለውጥ እርምጃን በመጠቀም ታማኝ፣ ፍትሐዊና ተምሳሌታዊ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሠልጣኞቹ የተከታተሉትን የተግባርና ንድፈ ሐሳብ ትምህርትና ሥልጠናም ሀገርና ሕዝብን በሚገባ ለማገልገል መጠቀም እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። 

የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት አክብሮ ማስከበርም ከተመራቂዎቹ የሚጠበቅ ሙያዊ መርህና ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ማረሚያ ኮሌጅ ዲን ረዳት ኮሚሽነር ተሻለ ሚቆሬ በበኩላቸው፤ የቀድሞው የፌዴራል ማረሚያ ማሠልጠኛ ተቋም ወደ ማረሚያ ኮሌጅነት ማደጉን አብስረዋል። 


 

ለዚህም ማሠልጠኛ ተቋሙን ወደ ኮሌጅ በማሸጋገር በተያዘው ዓመት በድህረ ዲፕሎማ ማሠልጠን እንደሚጀምር አስታውቀዋል። 

ተቋሙን ወደ ኮሌጅነት ለማሸጋገር በተደረገው ዝግጅትም በሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ በማረም ማነጽ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በዲግሪ መርሃ ግብር ሥልጠና እንደሚጀምር ተናግረዋል። 

ኮሌጁ ብቁ የሰው ኃይል ከማፍራት ባሻገር በምርምር መስክም ለሀገር የሚጠቅሙ ሥራዎችን ለማከናወን በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል። 

ሀገር የሚጠቅሙ የታረመና የታነጸ ዜጋ ለማውጣት በሚደረገው ጥረት ብቁ አመራርና አራሚ ባለሙያ ለማፍራት ኮሌጁ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በላቀ ደረጃ እንደሚፈጽም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም