ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል የምርታማነት አቅምን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ሀረር፣ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል የምርታማነት አቅምን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር ገለጹ።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ በክልሉ ሶፊ ወረዳ ቂሌ ቀበሌ በመገኘት የዘንድሮውን የበጋ መስኖ ልማት በይፋ አስጀምረዋል።


 

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሮዛ ኡመር እንዲሁም ሌሎች የክልሉ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ሃላፊ ሮዛ ኡመር፤ በክልሉ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል ብለዋል።

በዚህም በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ለአርሶ አደሮች የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮች፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች እና ሌሎችንም በማሟላት ለተሻለ ስኬት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጋ መስኖ ስንዴን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎች እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ይከናወናል ብለዋል።


 

ከዘመናዊ የከርሰ-ምድር ውኃ አጠቃቀም ጋር በማቀናጀት በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ የማምረት ልምድ እየዳበረ መምጣቱን ያነሱት ምክትል ርእሰ መስተዳድሯ ዘንድሮም  ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በክልሉ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም