አረንጓዴዋ ኢትዮጵያ- የኮፕ 32 አስተናጋጅና የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ማዕከል - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴዋ ኢትዮጵያ- የኮፕ 32 አስተናጋጅና የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ማዕከል
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው የአየር ንብረት መዛባት የሰው ልጅ ሕልውና ፈተና በሆነበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የዓለም አቀፉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) በኢትዮጵያ የሚካሄድ መሆኑ ልዩ ትርጉም ያለው ክስተት ነው።
ይህ ውሳኔ ኢትዮጵያ ለአካባቢ ጥበቃ ያሳየችውን ጠንካራ ቁርጠኝነትና በተግባር ያረጋገጠችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ዓለም አቀፍ እውቅና ያጎናጸፈም ነው።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የሰጠችው ተግባራዊ ምላሽም በፅንሰ-ሀሳብ ላይ ብቻ ሳይሆን በተግባር በተገለጡ ተጨባጭ ስኬቶች የተደገፈ ነው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት የዘንድሮውን ሳይጨምር ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ፣ የደን ሽፋንን ማሳደግና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያስቻሉ አርአያነት ያለው ተግባር አከናውናለች።
ከዚሁ ጎን ለጎን፣ ከተሞችን ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ምቹ የሚያደርጉ የአረንጓዴና ኮሪዶር ልማት ስራዎች የዜጎችን ህይወት ከማሳደግ ባሻገር ለአካባቢ ጥበቃ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።
በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት ማለትም በውሃ፣ በንፋስ፣ በፀሐይና በጂኦተርማል ኃይል ማመንጨት የምታደርገው ሰፊ ኢንቨስትመንት የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ለሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ከሚመነጨው ኃይል 99 በመቶ የሚሆነው ንጹህና አረንጓዴ ነው። ይህን ንጹህ ኃይል መነሻ በማድረግም ሀገሪቱ የነዳጅ ጥገኝነትን የሚቀንሱና አካባቢን የማይበክሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን (Green Mobility) በስፋት ወደ ጥቅም በማስገባት በኩል አብነት ያለው የፖሊሲ እርምጃ ወስዳለች።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በፈረንጆች 2027 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤን (COP32) ስታስተናግድ፣ "ታዳጊ ሀገራት በገንዘብ እጥረት ወይም በነዳጅ ቀውስ ሳይገደቡ እንዴት በፍጥነት ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ መሸጋገር ይችላሉ?" ለሚለው ትልቅ ጥያቄ ተግባራዊ ማሳያ እንደምትሆንም በቅርቡ ብሉበርግ ባሰራጨው ዘገባ ማመላከቱ አይዘነጋም።
በመሆኑም ኮፕ 32ን ማስተናገድ ለኢትዮጵያ ከዲፕሎማሲያዊ ስኬት ባሻገር ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲና ኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆን መንገድ ይከፍታል።
የኢትዮጵያ ተሞክሮም ለተሻለችና አረንጓዴዋ ምድር ትልቅ ተስፋ የሚሆን ነው።
የኮፕ 32 ይፋዊ ድረ-ገጽ https://cop32ethiopia.et/ ይጠቀሙ