በመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ የሚያስችሉ የአመራር አቅም ግንባታ እና ስልጠና ተቋማት ተፈጥረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ የሚያስችሉ የአመራር አቅም ግንባታ እና ስልጠና ተቋማት ተፈጥረዋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ):- በመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ የሚያስችሉ የአመራር አቅም ግንባታ እና ስልጠና ተቋማት መፈጠራቸውን በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስተባባሪ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ።
"ዕድገትን መምራት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።
ከዚህም ባሻገር የአፍሪካ የፖለቲካ ፖርቲዎች የብሔራዊ ልማት ሞተሮች በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፓናል ውይይት ተደርጓል።
በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስተባባሪ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ወሳኝ ሚና አላቸው።
ፓርቲዎች ከወቅታዊ የምርጫ ዝግጅት ባሻገር ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለዘላቂ ልማት መትጋት አለባቸው ሲሉም ገልጸዋል።
የፓርቲ ሥራ የማራቶን ሩጫ እንጂ በአንዴ የሚጠናቀቅ አይደለም ያሉት ዶክተር ደረጀ፤ ኢንቨስትመንት ቋሚ ግባቸው ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።
ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያሉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን አቅም ማጎልበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በየደረጃው ያሉ መሪዎችን ከማሰልጠን ባለፈ ለአፍሪካውያን ጭምር ክፍት ማድረጓን ገልጸዋል።
ከአፍሪካ አመራር ልሕቀት አካዳሚ ባሻገር በሁሉም ክልሎች የአመራር አቅም ማሻሻያ የስልጠና ማዕከላት መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ የሚያስችሉ የአመራር አቅም ግንባታና ስልጠና ማዕከላት እንዲስፋፉ ማስቻሉንም ተናግረዋል።