በጤናው ዘርፍ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጤናው ዘርፍ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል
ሆሳዕና ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ) ፡-በጤናው ዘርፍ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
28ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ" እመርታዊ ሪፎርም ለሉዓላዊና የማይበገር የጤና ስርዓት !!" በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት ዘመኑን የዋጀ የጤና ስርዓትን መገንባት የተወዳዳሪነት አቅምን ለማሳደግ ያግዛል።
የመደመር መንግሥት በሽታን ከመከላከል በተጨማሪ አክሞ ማዳንን መሰረት ያደረገ ስትራቴጂ በማዘጋጀት የጤናውን ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችል ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት በጤናው ዘርፍ የማህበረሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል።
በዚህም አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ተቋማት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አንስተው ከጤና ተቋማት ግንባታ በተጨማሪ የህክምና ቁሳቁሶችን በማሟላት ረገድ የማህበረሰቡ ተሳትፎ እያደገ መጥቷል ብለዋል።
በክልሉ በዘርፉ አሰራሮችን በማዘመንና እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጤናው ዘርፍ በሽታን አስቀድሞ በመከላከልና በማከም ረገድ በተከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ወደ 87 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከልና በማከም እረገድም ውጤት መመዝገቡን አመልክተዋል።
የጤና አገልግሎቱን በዲጅታል ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ፍትሀዊና ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች 226 የጤና ተቋማትን ከወረቀት ንኪኪ የፀዳ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ጠቁመዋል።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እንደገለፁት በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ፍትሀዊ ለማድረግ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ተሰፋ ሰጪ ዉጤት እየተመዘገበ ይገኛል።
በዲጅታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የጤና አገልግሎት በመስጠት ረገድም በክልሉ በሚገኙ 13 ሆስፒታሎችን ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ንኪኪ ነፃ ስለመደረጉ ጠቅሰዋል።
በጤናዉ ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማዘመን የተገልጋዩን እንግልት በማስቀረት እረገድ እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
በጉባኤው ላይ የፌዴራል ፣ የክልል ፣የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የጤና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።