በክልሉ ዘመናዊና የተቀናጀ የግብርና ልማትን በመተግበር የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ዘመናዊና የተቀናጀ የግብርና ልማትን በመተግበር የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል
አርባ ምንጭ፣ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊና የተቀናጀ የግብርና ልማትን በመተግበር የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
"የውሃ ፀጋችንን አሟጠን በመጠቀም ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርናን እውን ለማድረግ እንሠራለን" በሚል መሪ ሃሳብ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የ2019 የመስኖ ልማት ንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ባደረጉት ንግግር የግብርና ዘርፉን በማዘመንና የምርት አማራጮችን በማስፋት ከተረጅነት የመውጣት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ርእሰ መስተዳድሩ በመልእክታቸው ምርታማነትን ማሳደግና የክልሉን ነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ዋነኛ ትኩረታችን ነው ብለዋል።
በክልሉ ሊለማ የሚችል እምቅ አቅም መኖሩን የጠቀሱት ርእሰ መስተዳድሩ የግብርና ልማትና ምርታማነትን የማሳደግ ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
የግብርና እና ገጠር ልማት ላይ በማተኮር ምርታማነትን የማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራንና የገቢ ምንጮችን የማስፋት ጉዳይ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ካርታ ካስኬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የመስኖ ልማት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በዘንድሮው የመስኖ ልማት ከ186 ሺህ ሄክታር በላይ የሚለማ መሆኑን ጠቅሰው የበጋ መስኖን ጨምሮ ሌሎችንም ለማልማት ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።