ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላምና አንድነትን የሚያጠናክር ትውልድ ለማፍራት ብሩህ ተስፋ ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል በዘላቂ ሰላምና በወንድማማችነት የተመሠረተ አንድነትን በመገንባት በዲጂታል ዓለምም አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ትውልድ ለማፍራት ብሩህ ተስፋ መፈጠሩን የትግራይ ቴሌቪዥን የቀድሞ ጋዜጠኛ ዳሞራ ያህያ ገለጸ።

ጋዜጠኛ ዳሞራ ያህያ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ፤ የክልሉ የቀድሞ ሁኔታና አሁን ያለው ሰላም የጨለማና የብርሃን ያህል ስለሚለያዩ ፈጽሞ ሊወዳደሩ አይችሉም ብሏል።

የትግራይ ሕዝብ ዋና ፍላጎት ሰላም መሆኑን የጠቆመው ጋዜጠኛ ዳሞራ፤ የፖለቲካ ጥያቄዎቹ በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲመለሱ እንደሚፈልግ ገልጿል።

ሕዝቡ ሰላሙን የሚያደፈርሱ አቋሞችን በተደራጀ መልኩ በመቃወም አካባቢውን መጠበቅ እንዳለበትም ነው ያመለከተው።

በትግራይ ክልል ለረጅም ዓመታት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው “የመስዋዕትነት ታሪክ” ከአሁን በኋላ መቆም እንዳለበት ጋዜጠኛው አስገንዝቧል።

ከአሁን በኋላ የሚያስፈልገን የመስዋዕትነት ትውልድ ሳይሆን የቴክኖሎጂ፣ የሰላም እና የአንድነት ትውልድ ነው ሲሉ አፅንዖት ሰጥቷል።

ይህንን ለውጥ በማፋጠን ረገድም የወጣቱ ሚና ቀዳሚና ወሳኝ ሊሆን እንደሚገባ ገልጾ፤ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ከሌሎች ወንድሞቻችን ጋር በጋራ መኖር እንደሚገባ ጋዜጠኛ ዳሞራ ተናግሯል።

በተጨማሪም በክልሉ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር በሁለት እግሩ ጠንክሮ እንዲቆም ማገዝ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ጠቁሟል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት ክልሉ እንደ ኮሪደር ልማት፣ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት እና ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ካሉ አገራዊ የልማት እንቅስቃሴዎች መነጠሉ አሳዛኝ እንደነበር ገልጿል።

ስለሆነም የትግራይ ሕዝብ እነዚህን ፕሮጀክቶች በእጅጉ እንደሚናፍቃቸውና በክልሉ ያሉ ከተሞችን የማልማት ትልቅ ቁጭትና ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁሟል።

በክልሉ የሚገኙ ከተሞች ያሏቸውን የልማት ፍላጎትና ቁጭት ወደ ተግባር በመቀየር ማልማት እንደሚቻል ጋዜጠኛው አብራርቷል።

የባላአደራ አስተዳደሩ አመራሮች ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረው ለልማት ከተጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትግራይ ክልልን መገንባት እንደሚቻል እምነቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም