በአማራ ክልል ለአርሶ አደሩ ዘመናዊ አኗኗር ለገጠር ኮሪደር ልማት ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ለአርሶ አደሩ ዘመናዊ አኗኗር ለገጠር ኮሪደር ልማት ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷል
ባህር ዳር፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት አርሶ አደሩን ከልማዳዊ አኗኗር ወደ ዘመናዊ ለመቀየር ለሚያስችሉ የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራዎች ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ መሬት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አዳነ መሐሪ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ ከከተሞች በተጨማሪ የገጠር ኮሪደር ልማት ኢኒሼቲቭ ተቀርጾ በውጤታማነት እየተተገበረ ይገኛል።
በዚህም የአርሶ አደሩን ልማዳዊ አኗኗር ወደ ዘመናዊነት ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም በ148 ቀበሌዎች 2 ሺህ 960 ሞዴል ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁን በተካሄደ እንቅስቃሴም የ146 ሞዴል ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በሩብ ዓመቱ 36ቱን ገንብቶ ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል።
በአንድ ቀበሌ 20 ሞዴል ቤቶች እየተገነቡ ሲሆን፣ ይህም ተበታትኖ የሚኖረውን አርሶ አደር ወደ አንድ ማዕከል በማሰባሰብ የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች መሰረተ ልማትን በተሟላ መልኩ እንዲያገኝ ለማስቻል እንደሚያግዝም አብራርተዋል።
ሞዴል ቤቶቹ ደረጃቸውን የጠበቁ ከመሆናቸውም በላይ፣ እያንዳንዱ ቤት በውስጡ ሳሎን፣ የልጆች፣ የእንግዳ መቀበያና የመኝታ ክፍሎችን ማካተቱን ገልጸዋል።
እንዲሁም በግቢው የእንስሳት ማድለቢያ፣ የዶሮ ማርቢያ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማልሚያ ቦታ፣ የሶላር ኢነርጂ፣ የባዮጋዝና ዘመናዊ መጸዳጃ ቤትን ያካተተ እንደሆነም አስረድተዋል።
ለመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታም ከመንግስትና ከበጎ አድራጊ ባለሃብቶች 42 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ተሰብስቦ ተግባር ላይ እየዋለ መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ ስለገጠር ኮሪደር ልማትና ሞዴል ቤቶች ግንባታ በቂ ተሞክሮ ወስዶ ተግባሩን በማስፋት የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን በተዋረድ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በገጠር ኮሪደር ልማት በእቅድ የተያዙ ሁሉንም ሞዴል ቤቶች ገንብቶ ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት ከጥር ወር ጀምሮ በተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት 981 ሞዴል ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል።