የግብርና ዘርፉን በማዘመን ምርታማነትን የማሳደግ ጥረት ለማሳካት የአልሚ ባለሃብቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ዘርፉን በማዘመን ምርታማነትን የማሳደግ ጥረት ለማሳካት የአልሚ ባለሃብቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው
ሀዋሳ፣ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፡- የግብርና ዘርፉን በማዘመን ልማቱን የማሳለጥና ምርታማነትን የማሳደግ ጥረት ለማሳካት የአልሚ ባለሃብቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሲዳማ ክልል ኢንቨስትመንት ፎረም፤ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የዓለም ምግብ ድርጅት ተወካዮች፣ የክልሉ አመራሮች፣ የተለያዩ ባለሀብቶች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።
በፎረሙ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር)፤ በአርሶና አርብቶ አደሮች ልማት ብቻ ምርታማነትን ማሳደግና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የማይቻል መሆኑን አንስተው ለዘርፉ ስኬት የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመሆኑም የግብርና ዘርፉን ይበልጥ በማዘመን ልማቱን የማሳለጥና ምርታማነትን የማሳደግ ጥረት በማገዝ ረገድ በተለይም የባለሀብቱ ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ልማት ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የማስፋፋትና ምርታማነትን የማሳደግ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማንሳት ለዚህም የሁሉም ጥረት ሊታከልበት ይገባል ብለዋል።
የግል ባለሀብቱን የመደገፍና በዘርፉ ልማትየማሳተፍ ጉዳይ በመደመር መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተናግረው አሁን ላይ በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስተሮች ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እየለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የግብርናውን ዘርፍ ስኬታማ ለማድረግ መንግስት ምቹና አስቻይ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ባለፈ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የገንዘብ ቢሮ ሃላፊ ዳዊት ሀዬሶ (ዶ/ር)፤ በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረው የዘርፉ ልማት እመርታዊ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ለግብርና ልማት አመች መሬት መኖሩን እንዲሁም ሰፊ የገበያ እድሎች መኖራቸውን አንስተው ሌሎች አልሚዎችም እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።