ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተተኪ ስፖርተኞች መፍለቂያ እንዲሆኑ ቅንጅታዊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ዲላ፣ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ):- ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተተኪ ስፖርተኞችና የብቁ ስፖርት ባለሙያዎች መፍለቂያ ማዕከላት እንዲሆኑ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር ገለጸ።

ማህበሩ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በዲላ ዩኒቨርሲቲ እያካሄደ ነው።


 

የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አባይ በላይሁን በወቅቱ እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲዎች የእውቀትና የጥናት ተቋማት ከመሆናቸው ባለፈ የተተኪ ስፖርተኞች መፍለቂያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ስፖርት በአካል፣ በስብዕናና በስነ ልቦና የተገነባ ትውልድ መፍጠሪያ መድረክ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ማህበሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስፖርት ፌስቲቫልን በማዘጋጀት ሀገራዊ ሰላም፣ አንድነትና አካታችነትን ማጎልበት መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተተኪ ስፖርተኞችና የብቁ ስፖርት ባለሙያዎች መፍለቂያ ማዕከላት እንዲሆኑ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ጉባኤው ተቋማዊ አቅምን ከማጎልበት ባለፈ የ2019 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል አዘጋጅና የማህበሩ ስራ አስፈጻሚዎች ምርጫን ጨምሮ ሌሎች አጀንዳዎች ላይ መክሮ ውሳኔ የሚያሳልፍ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስፖርት ፌስቲቫል ትልቅ ሀገራዊ እሴት ነው ያሉት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ቶሎሳ ዲዳ (ዶ/ር) ናቸው።

በተለይ የተማሪዎችና የባለሙያዎች ስፖርት አቅምን ከማጎልበት ባለፈ ለባህል ልውውጥና ለሰላም እሴት ግንባታ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በማህበሩና በፌስቲቫሉ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገራዊ አንድነት መጎልበት የበኩሉን እንደሚወጣም አንስተዋል።

በጉባኤው የሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች፣ አጋርና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም