የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ የሕዝብና የሀገርን ሃብት በውጤታማነት መምራት እያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ የሕዝብና የሀገርን ሃብት በውጤታማነት መምራት እያስቻለ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ) ፦የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ሥርዓት የሕዝብና የሀገርን ሃብት በውጤታማ አስተዳደር መምራት እያስቻለ መሆኑን የኢፌዴሪ መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በተሻሻለው የመንግሥት ግዥና ንብረት አዋጅ፣ የአሠራር መመሪያና የዲጂታል ሥርዓቶች ላይ በቢሾፍቱ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ነው።
መድረኩም የግዥና የንብረት አስተዳደር ውጤታማነትን በማሳደግ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው የአፈጻጸም ሥርዓት በመዘርጋት ልምድን ለመለዋወጥና የቀጣይ የጋራ ሥራን ለመወሰንም ያለመ ነው።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ እንዳሉት፤ ባለሥልጣኑ የግዥ ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ በማድረግና በማዘመን ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ አሠራር ተግብሯል።
በግዥና ንብረት አስተዳደር የተያዘው ሀገራዊ ርዕይ ለማሳካት የተቋማትን አቅም፣ እውቀትና ልምድ በመደመር እሳቤ በማቀናጀት ውጤታማ ሥራን ማሳለጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
የመደመር እሳቤ የፈጠረው የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓትም በፌዴራል ተቋማት የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ተግባራዊ የሆነበትን ዕድል ፈጥሯል።
የመንግሥት ግዥ የሀገርና ሕዝብን ሀብት በብቃት ለመጠቀም፣ የልማት ግቦችን ለማሳካትና የሕዝብ አገልግሎትን ለማሻሻል ወሳኝ ስትራቴጂያዊ መሣሪያ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥን (e-GP) የአሠራር ሥርዓቱንም ከፌዴራል ተቋማት አልፎ ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በማስፋት ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል።
ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር የተጣጣመ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግም የተቋማትን አቅም በማሳደግ የዲጂታል ሥራዎችን ውጤታማነት ለማላቅ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።
የግዢና ንብረት አስተዳደር አዋጁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ያለው ውጤታማ የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት ወሳኝ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም የራሳቸውን የሕግና የአሠራር ማዕቀፍ እንዲያዘጋጁ የሚያግዝ ሞዴል መመሪያ ሥርዓት መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
በቀጣይም የፌዴራል፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ተቋማትን ቅንጅት በማጠናከር የዲጂታል ግዥ ሥርዓት ማስፋፋት፣ የተቋማትን አቅም ማጎልበት፣ የአፈጻጸም ክትትልና ተጠያቂነትን መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።