በከተማው በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የዓሳ እርባታ ሥርዓተ ምግብንና የገቢ ምንጭን እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የዓሳ እርባታ ሥርዓተ ምግብንና የገቢ ምንጭን እያሳደገ ነው
ጂንካ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፡- በጂንካ ከተማ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የዓሳ እርባታን ውጤታማ በማድረግ ሥርዓተ ምግብን ከማጎልበት ባሻገር የገቢ ምንጭን እያሳደገ መሆኑን በዓሳ ዕርባታ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ተቋማት ገለጹ።
የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የዜጎችን የአመጋገብ ስርዓት በማሻሻል በገበታቸው የተመጣጠነ ምግብ መመገብ እንዲችሉ እገዛ እያደረገ ነው።
በጂንካ ከተማ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በዓሳ እርባታ ስራ የተሰማሩ ግለሰቦችና ተቋማትም በመርሐ ግብሩ አማካኝነት በዘመናዊ መልክ የሚያከናውኑት የዓሳ እርባታ ስራ ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ተጠቃሚዎቹ አክለውም፣ በከተማው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የዓሳ እርባታን ውጤታማ በማድረግ ስርዓተ ምግብንና የገቢ ምንጭን እያሳደገ ነው ብለዋል።
የኔሪ ወንዝን በመጥለፍ በከተማው በአነስተኛ ቦታ ላይ በዘመናዊ መልክ የዓሳ እርባታ ስራን እያከናወነ የሚገኘው የጂንካ ከተማ ነዋሪው ሙሴ ሽፈራው፣ በከተማ ግብርና በተፈጠረለት ግንዛቤ በ2000 የዓሳ ጫጩቶች የጀመረው የእርባታ ስራ ውጤታማ እንዳደረገው ገልጿል።
የከተማው ግብርና ጽህፈት ቤት ከውሃ ገንዳ አዘገጃጀት፣ ከዓሳ እንክብካቤ፣ አያያዝና አመጋገብ ላይ ስልጠና ማግኘቱን ጠቁሞ፣ በጊቢው ዓሳ በማርባት ለግለሰቦችና ለተቋማት የዓሳ ጫጩቶችን በማከፋፈል ጭምር ገቢ እያገኘ መሆኑን ተናግሯል።
አሁን ላይ የዓሳዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ጠቁሞ፣ ለተቋማት ጫጩቶችን በማቅረብ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጿል።
በከተማው በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በዓሳ እርባታ ስራ ላይ ከተሰማሩ ተቋማት የጂንካ ማረሚያ ተቋም አንዱ ሲሆን፣ የተቋሙ አዛዥ ኮማንደር አስቻለው ነሬሬ የዓሳ እርባታው ከታራሚዎች አልፎ ለአካባቢው ማህበረሰብ ጥቅም እየሰጠ ነው ብለዋል።
ታራሚዎች በአነስተኛ ዋጋ ዓሳ በመግዛት መመገብ እንዲችሉ መደረጉን ጠቁመው፣ በዓሳ እርባታው ላይ የተሰማሩ ታራሚዎችም ለአካባቢው ማህበረሰብ ጭምር ዓሳ በማቅረብ ገቢ እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።
የጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በበኩሉ በጊቢው ለተግባር ልምምድ እገዛ እንዲያደርግ በዘመናዊ መልክ የዓሳ እርባታ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የኮሌጁ ዲን አቶ ካሳሁን ጌታቸው ናቸው።
ኮሌጁ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተግባር የተደገፈ ትምህርት በመስጠት የግብርና ስራውን ለማዘመንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በጂንካ ከተማ አስተዳደር ግብርና ዩኒት የዓሳ እርባታ ስራ ሂደት ባለሙያ ሳሊማ ከድር፣ በከተማው ዘጠኝ የሚሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች በዓሳ እርባታ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ጠቁመዋል።
በአካባቢው ከዚህ ቀደም የዓሳ እርባታ ስራ እምብዛም እንደማይታወቅ ጠቅሰው፣ አሁን በተቋማትና ግለሰቦች የዓሳ እርባታ ስራው እውቅና እያገኘ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዓሳ እርባታ ላይ የክህሎት ስልጠና በመስጠት ግለሰቦችንና ተቋማትን የማብቃት ስራ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፣ ከሌሎች አካባቢዎች የዓሳ ጫጩቶችን ጭምር በማምጣት ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም አስረድተዋል።