ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ከ23 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሩዝ ምርት ይጠበቃል

ጅማ፣ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፡-  በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን እየተሰበሰበ ካለው የሩዝ ሰብል ከ23 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።


 

የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቲጃኒ ተማም ለኢዜአ እንደገለፁት፣  በዞኑ በ2018/19 ምርት ዘመን መኸር ወቅት ከ594 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ ሰብል ለምቷል።

አሁን ላይ በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች የደረሰ የሩዝ ሰብል የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የሩዝ ሰብል የመሰብሰብ ሥራው በኮምባይነር የታገዘ በመሆኑ የምርት ብክነትን ለመከላከል ያስችላል ብለዋል።

በዞኑ በመኸር ወቅቱ ከለማውና በመሰብሰብ ላይ ካለው የሩዝ ሰብል ከ23 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።


 

በዞኑ ሊሙ ኮሳ ወረዳ ሩዝ ከሚያለሙ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ናስር ጀማል፣ የሩዝ ልማቱ ከመጀመሪያው ጀምሮ በጥንቃቄና በባለሙያዎች ድጋፍ መከናወኑ ለሰብሉ ጥሩ ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

ሰብላቸው በጥሩ ሁኔታ አድጎ እየተሰበሰበ መሆኑን የጠቀሱት አርሶ አደሩ፣ ከሩዝ ልማቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

አርሶ አደር ፀጋዬ ሰይፉ በበኩላቸው፣ ሩዝን በተደራጀ መንገድ ማልማታቸው ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደገው አመልክተዋል።

በዘንድሮው ዓመት የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ጠቅሰው፣ በግብርና ጽሕፈት ቤት ድጋፍ ምርቱ በኮምባይነር የሚሰበሰብ መሆኑ ያለብክነት ለገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም