አዳዲስ መሠረተ ልማቶች የመዲናዋን የትራንስፖርት ሥርዓት አዘምነዋል - ኢዜአ አማርኛ
አዳዲስ መሠረተ ልማቶች የመዲናዋን የትራንስፖርት ሥርዓት አዘምነዋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የተገነቡ የተለያዩ ዘመናዊ የመሠረተ ልማት አውታሮች የመዲናዋን የትራንስፖርት ሥርዓት ማዘመናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ።
የመደመር መንግሥት ለከተሞዋ ልማት በሰጠው ትኩረት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።
በተለይም የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተሞችን የቀድሞ ገጽታ በመቀየር ለዜጎች ምቹ፣ ጽዱ እና ተስማሚ አኗኗርን መፍጠር ችለዋል።
የዚህ በጎ ለውጥ ዋና አብነት የሆነችው አዲስ አበባ ከተማ፣ ቀደም ሲል በእግረኛ መንገድ እና በፓርኪንግ እጥረት ምክንያት ያጋጥሙ የነበሩ የትራፊክ አደጋዎችን በከፍተኛ ደረጃ መቅረፍ ተችሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው ለኢዜአ እንዳሉት፣ በመዲናዋ የተከናወኑ ፈጣን እና አስደናቂ የልማት ሥራዎች ተስማሚ እና ደህንነቷ የተረጋገጠ ተመራጭ ከተማ አድርጓታል።
በተለይም በኮሪደር ልማት ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች መገንባታቸው በእግር የመጓዝ ልምድን በማዳበር አዲስ የህይወት ዘይቤን አምጥቷል ብለዋል።
ይህም ለጤና፣ ለወጪ እንዲሁም ለአየር ብክለት መቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በከተማዋ ያልተለመዱ እንደ ስኩተርና ሳይክል የመሰሉ የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎቶች አሁን ላይ በስፋት መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል።
እነዚህ አዳዲስ አማራጮች የነዋሪዎችን የትራንስፖርት እንግልት ከመቅረፋቸው ባሻገር አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የተከናወኑት የልማት ሥራዎች የከተማዋን የትራንስፖርት አማራጮች በማስፋት የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት እያቃለሉ ይገኛሉ ብለዋል።
በከተማዋ ቀደም ሲል ከሁለት የማይልበጡ ፓርኪንጎች ብቻ የነበሩ መሆኑን አስታውሰው፣ አሁን ግን በአንድ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ በርካታ ፓርኪንጎች መገንባታቸውን አብራርተዋል።
ይህም ተሽከርካሪዎች አለአግባብ በመንገድ ላይ በመቆም ያጋጥም የነበረውን የትራፊክ አደጋ መከላከሉን አንስተዋል።
አሁን የተገነቡት የህንፃ ሥር ተርሚናሎች እና ዘመናዊ ፓርኪንጎች በአደጉት አገሮች እንደሚታየው የከተማዋን መልክ በማስተካከል የትራፊክ ደኅንነትን ማረጋገጥ ችለዋል ብለዋል።
እነዚህ አዳዲስ መሠረተ ልማቶች የከተማዋን የትራንስፖርት ሥርዓት ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ ረገድ ትልቅ ለውጥ እያመጡ መሆኑን አቶ ዳኛቸው አረጋግጠዋል።
እግረኞች በሚበዙባቸው ስፍራዎች ከመሬት በታች መተላለፊያዎች መገንባታቸውን ገልጸው፤ ይህም የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ ደኅንነቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።