በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት እያስገኘ ያለውን ውጤት በተሻለ ለማስቀጠል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት እያስገኘ ያለውን ውጤት በተሻለ ለማስቀጠል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ሊጠናከር ይገባል
ሀዋሳ ፣ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት እያስገኘ ያለውን ውጤት በተሻለ ለማስቀጠል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ሊጠናከር እንደሚገባ ተመላከተ።
የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ማጠናከርን ያለመና በሀዋሳና በመቐለ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በኖርዌይ መንግስት ትብብር የተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ ተካሄደ።
በወቅቱም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት አማካሪና የመርሃ ግብሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መብራቱ ሙላቱ፣ የምግብ ሥርዓትን ለማጠናከር የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የሚያግዙ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ያካተቱ 21 ምርምሮች በጉባኤው ላይ መቅረባቸውን ተናግረዋል።
ጥናቶቹ የጥራጥሬ እህሎችንና የእንስሳት ተዋጽኦ የምግብ ዓይነቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው በዚህ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን በማመላከት መፍትሔ ለማምጣት የሚያግዙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማኅበረሰብ ተሳትፎ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኢያሱ ግዛው በበኩላቸው፣ አሁን ላይ የምግብ ሥርዓትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ እየተገኙ ያሉ ውጤቶችን የበለጠ ለማጠናከር የባለድርሻ አካላት ተግባር ላይ ያተኮረ አካሄድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ሁናቸው በየነ፣ ንቁና አምራች ማኅበረሰብን ለመፍጠር ጤናማ የምግብ ሥርዓትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የምግብ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ከበደ አበጋዝ በበኩላቸው፣ የምግብ ሥርዓትን ለማጠናከር እንደ ሀገር አሰባጥሮ ማምረትና አጠቃቀም ላይ ያለውን ክፍተት መሙላት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
በምርምር ኮንፈረንሱ ላይ የዘርፉ ከፍተኛ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።