ቀጥታ፡

የዲጂታል ዘመንን የዋጀ የንባብ ባህልን ለማዳበር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ

‎ሀዋሳ ፤ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፡- የዲጂታል ዘመንን የዋጀ የንባብ ባህልን ለማዳበር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ባለሥልጣን ገለፀ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ባለሥልጣን ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና ከሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር "ንባብ ብቁ ሰው ያደርጋል" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የንባብ ሳምንት፣ የመጻሕፍት ሽያጭና አውደ ርዕይ ዛሬ በሀዋሳ ተካሄዷል።


 

በወቅቱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰርጸ ፍሬ ስብሀት እንደገለጹት፤ የዲጂታል ዘመንን የዋጀ የንባብ ባህልን ለማዳበር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ባለሥልጣኑ ለ83 ዓመታት ያከማቻቸውን የጽሑፍ፣ የምስልና የድምፅ ሀብቶች በዲጂታል መንገድ ማደራጀቱን ጠቁመው ይህም በውስን ቦታ ብቻ ይገኝ የነበረውን መረጃ ለአንባቢያንና መረጃ ፈላጊዎች ባሉበት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችልም አስረድተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ባለሥልጣኑ ትውልዱ የጥልቅ ንባብ ልምድ እንዲያዳብር በተለያዩ አካባቢዎች የንባብ ሳምንትና የመጻሕፍት አውደ ርዕይ እንዲሁም ሌሎች መርሃ ግብሮችን ከተባባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ፍስሀ ጌታቸው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መጻሕፍት የትናንት ተሞክሮን ከዛሬ ጋር የሚያገናኙና የነገን ዓለም እንድንገነባ መሠረት የሚጥሉ መሣሪያዎቻችን ናቸው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በንባብ ሳምንትና በመጻሕፍት አውደ ርዕይ መርሀ ግብሩ ላይ በትብብር መሥራቱ የያዛቸውን ቁልፍ ተልዕኮዎች የሚያሳካበት አንዱ መንገድ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው አረጋግጠዋል።

የንባብ ባህልን ማሳደግ የአንድ ተቋም ብቻ ኃላፊነት ባለመሆኑ፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ደራሲያን፣ አሳታሚዎች፣ ወላጆችና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል።

የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢሺኔ ሀንቃሎ (ዶ/ር)፣ ክልሉ የተለያዩ የባህል፣ የሥነ ቃል፣ የሥነ ጥበብና ሌሎች ሀብቶች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው፣ በተደራጀ መንገድ ተሰንደው ለትውልድ እንዲተላለፉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

በክልሉ በየአካባቢው ያሉ ቤተ መጻሕፍትን የማጠናከር ሥራ ቢሮው በልዩ ትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ ደራሲያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም