የመደመር እሳቤ የአፍሪካውያንን ወንድማማችነት ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ የአፍሪካውያንን ወንድማማችነት ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ):-የመደመር እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ሀገራትን አንድነትና ትብብር በማጠናከር የህዝቦችን ወንድማማችነት ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ሥራ ላይ የዋለው የመደመር እሳቤ በሁሉም መስክ ውጤት እያመጣ ነው።
መደመር ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካም ትልቅ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን አንስተው፤ በአፍሪካ ደረጃ የዜጎችን ህይወት የሚቀይሩ እሳቤዎችን ሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
በአፍሪካ አብላጫ ድምጽ አግኝተው የሚመሩ ፓርቲዎች በሚመሰርቱት መንግሥት የህዝቦቻቸውን ህይወት ለመለወጥ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በጉባኤው ላይ በኢትዮጵያ የመደመር እሳቤ ትግበራ የመጡ ለውጦች ቀርቦ የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ እየወሰዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የመደመር እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ሀገራትን አንድነት፣ ትብብር እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማስተናገድ ላይ የምትገኝ መሆኑን አንስተው፤ ከ250 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በአገራችን መካሄዳቸው ኢትዮጵያ ለሰላም እና ለጉባኤዎች ያላትን ተመራጭነት ያሳያል ብለዋል።
የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማነቃቃት፣ ለአፍሪካ ሀገራት ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲሁም የዲፕሎማሲ ስራዎችን ከማጠናከር አኳያም ጉባኤው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።
ጉባኤው ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ መሪዎች አዲስ አበባን የመጎብኘት እና በከተማው የተከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን የመመልከት እድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።