ቀጥታ፡

የዕድገት መሻቷን የምታሳካ ወደ ብልጽግናዋ የምትገሰግስ ሀገር

ኢትዮጵያ ፈተናዎችና ተግዳሮቶችን በአይበገሬነትና በብቃት በመሻገር፣ በታቀዱ እና ስትራቴጂካዊ በሆኑ ሀገራዊ ፕሮግራሞች አማካኝነት ውጥኖቿን በተግባር ማሳካት የምትችል ታላቅ ሀገር መሆኗን እያረጋገጠች ትገኛለች።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ያስመዘገበቻቸው ሁለንተናዊ ድሎች፣ ታላላቅ ራዕዮች ወደ ተጨባጭ ውጤት መለወጥ እንደሚችሉ ማሳያ ናቸው። ሀገሪቱ በኢኮኖሚ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በመሠረተ ልማትና በአቪዬሽን ዘርፎች ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች የዚህ ማረጋገጫዎች ናቸው።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም አማካኝነት የተመዘገበው ስኬት የሀገሪቱን የመፈጸም አቅም በግልጽ ያሳያል። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አጠቃላይ የሸቀጦች ወጪ ንግድ ባለፈው በጀት ዓመት 11 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ ይሄም  ለ17 ዓመታት የተገኘውን ገቢ ድምር (ማለትም ከ1984 እስከ 2000 ዓ.ም) ያለውን በአንድ ዓመት ብቻ ያሳካም ነው ። የተወሰደውን የፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከሃያ እጥፍ በላይ ዕድገት አሳይቷል።

በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው ምርታማነት ዕድገት ሀገሪቱ ከጥገኝነት ተላቃ ራሷን መቻል እንደምትችል ያሳየችበት ሌላው ስኬት ነው። ኢትዮጵያ ለብዙ አሥርት ዓመታት ስንዴን ከውጭ በዕርዳታና በግዢ ታስገባ የነበረ ቢሆንም፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ባደረገችው ከፍተኛ ርብርብ ራሷን ችላ ምርቱን ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች። በተጨማሪም በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በተከናወኑ ዘመናዊ የግብርና ሥራዎች ለስርዓተ ምግብ መጠናከር የበኩሉን ሚና እየተወጣም ይገኛል።

ይሄንን ተሞክሮዋን ለአፍሪካውያን እና ለተለያዩ የዓለም ክፍሎች እያጋራች ትገኛለች ። በተጨባጭ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣትም  የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ለሚሹ አካላት የስኬቷን እንዴትነት እያሳየች ልምዷንም ታካፍላለች። ከሳምንታት በፊት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የኢትዮ ናይጄሪያ የስነ ምግብ አመራር የልምድ ልውውጥ/Nigeria-Ethiopia Nutrition Leadership Exchange/ ለማድረግ የመጡትን የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ እና ልኡካቸውን ጨምሮ የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ተሞክሮ ወስደዋል።

ይህ በግብርና የታየው አቅም በአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭም ተደግሟል። ባለፉት ስምንት ዓመታት በመርሐ ግብሩ አማካኝነት ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ በአንድ ጀምበር ብቻ ከ26 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በማሳተፍም 805 ነጥብ3 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አስደማሚ ስኬት ተመዝግቧል። ይህ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ የሀገሪቱን የደን ሽፋን ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ከፍ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን በተጨባጭ መከላከል እንደሚቻል በተግባር አስመስክሯል።

የግዙፍ መሠረተ ልማቶች ግንባታ አፈጻጸም ኢትዮጵያ የጀመረችውን ዳር ማድረስ የምትችል ፅኑ ሀገር መሆኗን ይመሰክራል። በኢትዮጵያውያን ገንዘብ፣ ጉልበትና ዕውቀት ተገንብቶ በአሁኑ ወቅት ኃይል ማመንጨት የጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ግንባታ ላይ የሚገኘውና 1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የኮይሻ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት የዚህ እውነት ሕያው ምስክሮች ናቸው።

በአቪዬሽን ዘርፍ የተመዘገቡት ዓለም አቀፋዊ ስኬቶችም የሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ ተወዳዳሪነት ይበልጥ የሚያጎሉ ናቸው። በ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ግንባታው የተጀመረው አዲሱ የቢሾፍቱ ሜጋ አየር ማረፊያ (BIA) የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመንገደኞች የማስተናገድ አቅም በዓመት ወደ 60 ሚሊዮን የሚያሳድግ ሲሆን፣ ይህም የሀገሪቱን የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከልነት ያጠናክራል።

ከዚህ ጎን ለጎን የዓለማችን ግዙፉ የአቪዬሽን ኩባንያ ቦይንግ (Boeing) የአፍሪካ አህጉራዊ ዋና መሥሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ መክፈቱ፣ ኢትዮጵያ ያሰበችውን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ማሳካት የምትችልና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተአማኒነት ያላት ሀገር መሆኗን በይፋ የሚያረጋግጥ ታላቅ ምዕራፍ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም