ቀጥታ፡

የመደመር እሳቤ በፓርቲዎች መካከል በትብብር የመሥራት አዲስ የፖለቲካ ባህል ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ):- የመደመር እሳቤ በፓርቲዎች መካከል የፖሊሲ ልዩነት ቢኖርም  በትብብር የመሥራት አዲስ የፖለቲካ ባህል መፍጠሩን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ በተካሄደ የፓናል ውይይት ወቅት እንደገለጹት፤ የመደመር መንግሥት የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ ምቹ ምኅዳር ፈጥሯል።

በዚህም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚኒስትርነት ጀምሮ በተለያየ ኃላፊነት ተሰማርተው ለሀገር ልማት በጋራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የመደመር መንግሥት የተለያዩ የፖለቲካ ሀሳቦችና አመለካከቶች ለኢትዮጵያ ዕድገት ጠቃሚ መሆናቸውን በመገንዘብ በትብብር እየሠራም መሆኑን ገልጸዋል።

የምርጫ ውጤትን በሰላም መቀበል አስፈላጊ መሆኑን አንስተው፤ የፖለቲካ ልዩነት ወደ ግጭትና አለመረጋጋት መምራት እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ ቢያሸንፍም፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳብ ለአገር ጠቃሚ በመሆኑ የመደመር መንግሥት የሥልጣን ድርሻ እንደሰጣቸው ገልጸዋል።

በምርጫው ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመሳተፍ የምርጫ ውጤቱን መቀበላቸውን አንስተው፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሐሳባቸው ወደፊት ሊያሸንፍ እንደሚችል እንዲያምኑ ማድረጉንም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያውያን ግጭት ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ መገንዘባቸውን አንስተው፤ ኢትዮጵያውያን ከግጭትና ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ ትምህርት ወስደዋል ብለዋል።

ፓርቲዎች ልዩነታቸውን ትተው በጋራ መሥራት እንደሚችሉ ሚኒስትር ዴኤታው አንስተው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የዚህ ትብብር አብነት መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ትብብር የተመዘገቡ የልማት ውጤቶችን ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም