በክልሉ በጤናው ዘርፍ የማኅበረሰቡንና አጋር አካላትን አቅም በመጠቀም የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በጤናው ዘርፍ የማኅበረሰቡንና አጋር አካላትን አቅም በመጠቀም የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ ነው
ሆሳዕና ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፡-በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጤናው ዘርፍ የማኅበረሰቡንና አጋር አካላትን አቅም በመጠቀም የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በሆሳዕና ከተማ ያስገነባው የኩላሊት እጥበት ማዕከልና ልዩ ክሊኒክ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በጤናው ዘርፍ የማኅበረሰቡንና አጋር አካላትን አቅም በመጠቀም የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ ነው።
ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በሆሳዕና ከተማ ያስገነባው የኩላሊት እጥበት ማዕከልና ልዩ ክሊኒክ አገልግሎቱን ለማግኘት ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን ችግርና እንግልት የሚፈታ ነው ብለዋል።
ከተቋሙ ጋር በቅንጅት መስራት የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚረዳ በመሆኑ፣ የክልሉ መንግስት ማዕከሉን በመደገፍ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፣ በኩላሊት ሕሙማን ላይ የሚደርስን ሁለንተናዊ ጫና ለመከላከል የቅድመ መከላከል ሥራን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከመከላከል በተጨማሪ ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚደግፉ እንደ ሜሪ ጆይ ያሉ ተቋማትን መደገፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በተቋሙ የሚከናወኑ የበጎ ተግባር ተግባራትን ለማጠናከር ሚኒስቴሩ በቅንጅት እንደሚሠራም አመልክተዋል።
የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ እንደገለጹት፣ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ አረጋውያንና ሕጻናትን ከማስጠለል በተጨማሪ በርካታ የበጎ ተግባር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ተቋሙ የኩላሊት እጥበት፣ ንቅለ ተከላና የካንሰር ሕክምና ማዕከላትን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በሆሳዕና ከተማ 5ኛውን የኩላሊት እጥበት ማዕከል ከፍቶ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ መቻሉንና ይህም የሕክምና አገልግሎቱን ለማግኘት ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ለእንግልት ሲዳረጉ የነበሩ ሕሙማንን ችግር የሚፈታ መሆኑን አንስተዋል።
በማዕከሉ የተጀመሩ የበጎ ተግባር ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የማኅበረሰቡ ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የሀዲያ ዞንና የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ አርቲስቶችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።