ቀጥታ፡

በመደመር ፍልስፍና በማዕድን ዘርፍ የተመዘገበው ዕመርታ የሀገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሽግግር ማሳያ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ በመደመር ፍልስፍና በማዕድን ዘርፍ የተመዘገበው ዕመርታ የሀገሪቱ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሽግግር ማሳያ መሆኑን የማዕድን ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

ከዚህም ባሻገር "የአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብት ከብዝበዛ ወደ ኢኮኖሚ አቅም" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፓናል ውይይት ተደርጓል።

የማዕድን ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብትና ማዕድናት ለብዙ ዓመታት የሌሎች ሀገራት የሀብት ምንጭ ሆነው ቆይተዋል።

አፍሪካ ያላትን የማዕድን ሀብት እሴት ከመጨመርና ከማቀነባበር ይልቅ ጥሬውን ወደ ውጭ እየላከች ስትበዘበዝ ኖራለች ብለዋል።

አፍሪካ የማዕድን ሀብት፣ አቅም፣ ካፒታል፣ ዕውቀት እንዳላት አስታውሰው፤ ነገር ግን ሀብቷን ሌሎች ሲጠቀሙበት እንደነበር ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷን እሴት በመጨመር፣ ወጣቶችን በክህሎት በማብቃትና በማቀነባበር ጥቅም ላይ ማዋል ጀምራለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ የማዕድን ማጣሪያ፣ የጋዝ ማምረቻ፣ የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክቶችን ሥራ ላይ ማዋል መጀመሯን ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሀብታችንን እሴት በመጨመርና በማቀነባበር ለውጭ ገበያ በማቅረብ ኢንዱስትሪው በፍጥነት እንዲያድግ ተደርጓል ብለዋል።

የማዕድን ማጣሪያ ፋብሪካው ለአፍሪካ የማዕድን ዘርፍ መነቃቃት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት ለውጭ ገበያ የነበረው የወርቅ ምርት በዓመት 300 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደነበር ገልጸው፤ በመደመር እሳቤ ዘርፉ እመርታ በማስመዝገብ ወደ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር አድርጓል ብለዋል።

የመደመር ፍልስፍና ያመጣው የሚታይና የሚጨበጥ ለውጥ የኢትዮጵያ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሽግግር ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በገጠርና በከተማ ኮሪደር ልማት፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ስምንት ሚሊዮን ሕፃናትን በቀን ሁለት ጊዜ በመመገብ በህዝብ ዘንድ እምነት የሚጣልበት ሥርዓት ተፈጥሯል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ወጣቶችን በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና በማብቃት ዜጎችን የልማቱ ተሳታፊ በማድረግ የሚታይና የሚጨበጥ ግልጽነት መፈጠሩንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም