የሀገርን ዕድገት ለማፋጠን ወጣቶችን በኃላፊነትና ውሳኔ አሰጣጥ በማብቃት አዳዲስና ተተኪ መሪዎችን ማፍራት አለብን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ዕድገት ለማፋጠን ወጣቶችን በኃላፊነትና ውሳኔ አሰጣጥ በማብቃት አዳዲስና ተተኪ መሪዎችን ማፍራት አለብን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ):- የሀገርን ዕድገት ለማፋጠን ወጣቶችን በኃላፊነትና ውሳኔ አሰጣጥ በማብቃት አዳዲስና ተተኪ መሪዎችን ማፍራት አለብን ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠንካራ መሪዎች ተተኪዎችን ማዘጋጀት ባልተቻለበት ወቅት ሀገራት የዕድገት ፍጥነታቸውን ሲያጡ ተመልክተናል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።
የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ የብልፅግና ፓርቲ በመደመር ፍልስፍና የተለያዩ አቅሞችን በማቀናጀት የህዝብን ጥንካሬ ለጋራ ዓላማ በማሰባሰብ አስደማሚ ስኬትን እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት በመደመር እሳቤ የተለያዩ ክልላዊ የፖለቲካ ድርጅቶች አንድ ሀገራዊ ፓርቲ ማምጣት እንደተቻለ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ወደ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን የብልፅግና ፓርቲ አባላት መሆናቸውን አስረድተዋል።
በዘንድሮው ምርጫም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚገኙት ወንበሮች 15 በመቶው ላይ እጩዎችን ላለማቅረብ በመወሰን የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን በማካተት አዲሱን የመደመር መንግሥት መስርተናል ብለዋል።
በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የፖሊሲ ልዩነትና የማያግባቡ ጉዳዮች ቢኖሩም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ከመስራት የሚያግድ ነገር እንደሌለ በተግባር ማስመስከር እንደተቻለ አንስተዋል።
ሕዝብን ማገልገል ከባድ የኢኮኖሚ ውሳኔዎችን መውሰድ ማለት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም በንግድና ኢንቨስትመንት ምርታማነትና የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም የቴሌኮምና የባንክ ኢንዱስትሪውን ለኢንቨስትመንት ክፍት በማድረግ በገበያ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ሥርዓት መፍጠር እንዳስቻለ አብራርተዋል።
በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታም ከ53 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት በማድረግ አርሶአደርና ተማሪን ጨምሮ ማንኛውም ዜጋ ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኝበትን ዕድል መፈጠሩን አንስተዋል።
መደመር ሌሎች የጀመሩትን ሥራ መገንባትንም ይመለከታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያደረጉትን ድጋፍ በመጠቀም ቆሞ የነበረን ፕሮጀክት ማጠናቀቅ እንደተቻለ አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም ንጋት ሐይቅን የፈጠረው ሕዳሴ ግድብ በመላው ኢትዮጵያና ለጎረቤት ሀገራት የተረፈ የኤሌክትሪክ ኃይል በረከት እየስገኘ መሆኑን አንስተዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም ባለፉት ዓመታት ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል፣ ጤናማ አፈርና አስተማማኝ የውሃ አቅርቦት መገንባት እየተቻለ መምጣቱን አንስተዋል።
ገዢውና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕዝቡ እድገታቸውን ሊከታተል በሚችልባቸው ግልጽ ምዕራፎች የተደገፉ የረጅም ጊዜ ግቦች ላይ መስማማት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ፖሊሲዎቻችን ሊለያዩ ይችላሉ፤ መራጮችም የሚፈልጉትን ይመርጣሉ፤ ነገር ግን ብሔራዊ ጥቅሞች መንግሥት ቢቀየርም ቀጣይነታቸውን ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል።
ተፎካካሪዎች ዕቅዱን እየተቹ ግቡን መደገፍ ይችላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ እቅድ እንዴት ይሰራል? ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል? ማንስ ይተገብረዋል? የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳት እንደሚችሉ አስረድተዋል።
መንግሥትም ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠትና ውጤቶችን ለማሻሻል እንደ መነሻ መጠቀም እንዳለበት አብራርዋል።
ጠንካራ መሪዎች አዳዲስና ተተኪዎችን ማዘጋጀት ባልቻሉበት ወቅት ሀገራት የዕድገት ፍጥነታቸውን ሲያጡ ተመልክተናል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ለወጣቶች ኃላፊነት በመስጠት ጥሩ የውሳኔ አሰጣጥ ብቃትና የታማኝነት ባህል መገንባት አለብን፤ ለዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ አስተዋጽኦ ታደርጋለች ብለዋል።
የልህቀት አካዳሚውም ስልጠናውን በመላው አህጉሪቷ ላሉ ሁሉም ፓርቲዎች ክፍት ማድረግን አብራርተዋል።