ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የዳኝነት ነጻነትና ተጠያቂነትን በሚዛናዊ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ):-በኢትዮጵያ የዳኝነት ነጻነትና ተጠየቂነትን በሚዛናዊ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት እየተገነባ መሆኑን የፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

በኢትዮጵያ የዳኝነት የሕግ ማዕቀፍ እና አተገባበር በሚል ርዕስ ኢንስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት ሲምፖዚየም አካሄዷል።


 

የፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በሲምፖዚየሙ ላይ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓቱ በብቁ የሰው ሃይል፣ በጠንካራ ተቋማት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በተደራጀ አሰራር እየተገነባ ይገኛል።

የዳኝነት ሙያ የአቋም ሥርዓትና የሞራል ልዕልና የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ዳኞች የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች የዜጎችን ነጻነት፣ የንብረት ባለቤትነት፣ የሰላምና የደህንነት እጣ ፈንታ የሚወስኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የዳኝነት ደህንነት የዳኞች ግላዊ መብት ብቻ ሳይሆን፣ የህዝብ ፍትህ የማግኘት እና በህግ ስርዓቱ ላይ ያለው እምነት መገለጫ መሆኑን አስረድተዋል።

ደህንነቱ የተጠበቀ የዳኝነት ስርዓት የሌለበት ሀገር የህግ የበላይነትን እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደማይቻል ገልጸዋል።

የዳኞች ደህንነት የሕግ ማዕቀፍ አተገባበር የግለሰብ ደህንነት ብቻ ሳይሆን የፍትህ ሥርዓቱ ደህንነት መጠበቅ እና የሀገር ማረጋጋት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም በኢትዮጵያ የነጻነትና ተጠያቂነት ሚዛናዊነትን የሚያስጠብቅ ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት እየተገነባ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ምትኩ ማዳ በበኩላቸው፤ የዳኝነት ደህንነት የሕግ የበላይነት፣ የዲሞክራሲ ስርዓት እና የሰብዓዊ መብቶች መከበር መሰረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዳኞች ያለምንም ፍርሃት፣ ዛቻና ጣልቃ ገብነት ሥራን ማከናወን እንዲችሉ ተገቢ የሆነ የደህንነት፣ ድጋፍና ክትትል እንዲደረግላቸው ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሲምፖዚየሙ በኢትዮጵያ የዳኝነት የሕግ ማዕቀፍ እና አተገባበር በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ዳኛ ቀነአ ቂጠታ፤ የሕግ ማዕቀፎች በማሻሻል ፍርድ ቤቶች ከማንኛውም ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው ፍትህን እንዲያሰፍኑ በማድረግ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።


 

የዳኞች ደህንነት በህግ ማዕቀፍ ማስደገፍ ቀልጣፋና ውጤታማ የሆነ የፍትህ ስርዓት እንዲኖር እንዲሁም ነጻነትና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ያደርጋል ብለዋል።

የፍትህ ተደራሽነት ለማሳደግ የዳኝነት ስርዓት ለማሻሻል ውጤታማ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዳኞች ደህንነት የሕግ ማዕቀፍ አተገባበር ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የዳኝነት ደህንነት ፅንሰ ሀሳብ፣ ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ዙሪያ ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት የህግ ባለሙያ አቶ ዳሳ ቡልቻ ናቸው።


 

የዳኝነት አካላት ነጻነት እና ደህንነት በተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የህግ ሰነዶች ውስጥ የተረጋገጠ መሠረታዊ መብት መሆኑን ገልጸዋል።

የዳኝነት ደህንነት ጽንሰ-ሀሳብ ዳኞች ውሳኔ በሚሰጡበት ወቅት ያለአንዳች ተጽዕኖ ነጻ የሚሆኑበትን ከባቢ መፍጠር፣ የፍትህ ጥራት ማረጋገጥ ላይ እንደሚያተኩርና ለተቋማዊ አሰራር የሚያገለግል መሆኑን አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም