ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓድዋ የተጎናጸፈችው ድል ለአፍሪካውያን የራስን ዕጣ ፈንታ የመወሰን ዘላቂ ማስታወሻ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያ በዓድዋ ሉዓላዊ ነጻነቷን በማስጠበቅ የተጎናጸፈችው ድል ለመላ አፍሪካውያን የራስን ዕጣ ፈንታ በራስ የመወሰን ዘላቂ ማስታወሻ መሆኑን የአፍሪካ አስተዳደር ማዕከል ሊቀ መንበር ቤኔዲክታ ላሲ ገለጹ፡፡

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

በዚሁ ወቅት የአፍሪካ አስተዳደር ማዕከል ሊቀ መንበር ቤኔዲክታ ላሲ፤ ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት፣ በኃይል፣ በኢንዱስትሪና በምርታማ ሥራዎች ላይ ኢንቨስት አድርጋለች ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገቷም በየጊዜው ለውጥ እያስመዘገበ መሆኑን በመጠቆም፤ ጉባኤው በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄዱ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በዓድዋ ሉዓላዊ ነጻነቷን በማስጠበቅ የተጎናጸፈችው ድል ለመላ አፍሪካውያን የራስን ዕጣ ፈንታ በራስ የመወሰን ዘላቂ ማስታወሻ መሆኑን አንስተዋል።

የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ለመንግሥት ሥራ መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

ምርጫ አንድ ፓርቲን በአንድ ጀምበር ሥልጣን ላይ ሊያስቀምጠው እንደሚችል ጠቅሰው፤ ሀገር ለመምራትና ኢኮኖሚን ለማስተዳደር የሚያስፈልገው ዕውቀት ግን በአንድ ጀምበር አይገኝም ብለዋል።

የፓርቲ ትምህርት ቤቶች፣ ኢንስቲትዩቶችና የምርምር መዋቅሮች ፓርቲዎች ሐሳቦቻቸውን እንዲፈትሹና ሰዎችን እንዲያዘጋጁ ጊዜ እንደሚሰጧቸው ገልጸዋል።

አፍሪካ ከፍተኛ የልማት ፋይናንስ ክፍተት እንዳለባት የገለጹት ሊቀ መንበሯ፤ በአህጉሪቷ ውስጥ ግን በቂ ሀብት እንዳለ አመልክተዋል።

ፓርቲዎች፣ የአስተዳደር ተቋማትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አጀንዳ 2063 እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት በብዙ ሀገራዊ ምርጫዎች ውስጥ እንደሚያልፉ በመግለጽ፤ ፓርቲዎች ስምምነቶቹን ቢረዱ ውሳኔዎቹ መንግሥት ቢቀየርም እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ፓርቲዎች የሴቶችንና የወጣቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ማላቅ እንዳለባቸው በማስገንዘብ፤ ጉባኤውን ላስተናገዱት የኢትዮጵያ መንግሥትና ብልፅግና ፓርቲ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም