የአዲስ አበባ ፈጣን እድገትና ዘመናዊ ገጽታ የዓለም አቀፍ ከተሞችን ደረጃ የሚያሟላ ነው - የዚምባቡያዌው ሴናተር ዳግላስ ምዎንዞራ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ፈጣን እድገትና ዘመናዊ ገጽታ የዓለም አቀፍ ከተሞችን ደረጃ የሚያሟላ ነው - የዚምባቡያዌው ሴናተር ዳግላስ ምዎንዞራ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ):-የአዲስ አበባ ፈጣን እድገትና ዘመናዊ ገጽታ የዓለም አቀፍ ከተሞችን ደረጃ የሚያሟላ መሆኑን የዚምባቡዌው ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ (Movement for Democratic Change) ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሴናተር ዳግላስ ምዎንዞራ ገለጹ።
ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱን ቀጥሏል።
የጉባኤው ተሳታፊ የሆኑት የዚምባቡዌው ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ (Movement for Democratic Change) ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሴናተር ዳግላስ ምዎንዞራ በኢትዮጵያ በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ የታየው የመሰረተ ልማት እና ሁለንተናዊ እድገት እጅግ የሚደንቅና ለአህጉሪቱ አገራት ከፍተኛ መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባኤውን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡት የፓርቲው ፕሬዝዳንት፤ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሱበት ቅጽበት ጀምሮ የተደረገላቸው አቀባበል እና እንግዳ ተቀባይነት እንዳስገረማቸው ተናግረዋል።
በተለይም በአገሪቱ እየተከናወነ ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ አስደናቂ ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጹት ተወካዩ፤ ከተማዋ ካደጉትና ከበለጸጉ አገራት ከተሞች ጋር የሚስተካከል ገጽታ እየተላበሰች መሆኗን መመልከታቸውን ነው ያመለከቱት።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበረውን ሁኔታ በማስታወስም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመዘገበው ይህ ፈጣን ለውጥ እጅግ እንዳስደነቃቸውና በኢትዮጵያ ያዩት ነገር ትልቅ ተስፋና መነሳሳትን የፈጠረባቸው መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም የመሰረተ ልማት ጥራቱ እጅግ የላቀ ከመሆኑም ባሻገር የአዲስ አበባ ከተማ እጅግ ንጹህ እና ውብ መሆኗ ትኩረታቸውን እንደሳበው ጠቅሰው፣ በቆይታቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ሴናተሩ ገልጸዋል።