የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የትግራይ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የምስክር ወረቀት ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የትግራይ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የምስክር ወረቀት ሰጠ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዲስ ስያሜ ህጋዊ እውቅና ለሰጠው የትግራይ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የምስክር ወረቀት ሰጥቷል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ የኮርፖሬሽኑን ብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የምስክር ወረቀት ለትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የፖለቲካ ጉዳዮችና የህዝብ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሃለፎም አስረክበዋል።
በትግራይ ክልል የህዝብ የመረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚሰሩ የሚዲያ ባለሙያዎችና አመራሮች አቅም ግንባታና መሰል የቴክኒክ ድጋፍ ዙሪያ በፅህፈት ቤታቸው የጋራ ውይይትም አካሄደዋል።
በውይይቱ ላይ አቶ ረዳኢ ሃለፎም የባለአደራ አስተዳደሩ በክልሉ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትን ለማምጣትና እንዲሁም የእድገትና የልማት ስራዎችን ለማፋጠን የሚያስችለውን የህዝብን የመረጃ ተደራሽነት ለማረጋገጥ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህ ወቅት ኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ድምፅ በመሆን አዎንታዊ ሚናውን በተገቢው እንዲወጣ ለሚያደርገው ጥረት ባለስልጣኑ የሚያደርገውን እገዛና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ባለሥልጣኑ በአዲስ ስያሜ ወደ ህዝብ ተደራሽ ለሆኑት የክልሉ ሚዲያዎች በአገራችን ህጎች፣ በብሔራዊ ጥቅም፣ በሰላም ግንባታ፣ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ እና በጋዜጠኝነት የሙያ ስነ ምግባር መዳበር አጋዥ በሆኑ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በአዲስ ባስገነባውና ትናንት ባስመረቀው የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
አክለውም ባለስልጣኑ በአዋጁ በተቀመጠው መሠረት በክልሉ ለህዝብ መረጃ ተደራሽነት በጎና አዎንታዊ አስተዋፅኦ ሚና ላላቸው ሚዲያዎች የቴክኒክና መሰል ድጋፎችን ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለኃላፊው ገልጸውላቸዋል።