በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስድስት ከተሞች የደረቅ ጭነት መናኸሪያዎች ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስድስት ከተሞች የደረቅ ጭነት መናኸሪያዎች ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ ነው
ዲላ፣ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስድስት ከተሞች የደረቅ ጭነት መናኸሪያዎች ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
የህዝብ መናኸሪያዎችን ደረጃ በማሻሻልና በማዘመን ለህዝብ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
በቢሮው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ብርሃኑ ጌቦ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በሎጅስቲክስ ዘርፍ የሚስተዋሉ ውሱንነቶችን ለመፍታት በስድስት የክልሉ ከተሞች የደረቅ ጭነት መናኸሪያዎች ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑንና በተያዘው በጀት ዓመትም አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ግንባታቸው እየተፋጠነ ካሉ መናኸሪያዎች መካከል የዲላ እና የጂንካ ከተሞች የደረቅ ጭነት መናኸሪያዎች በቀጣይ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉ ብለዋል።
የተቀሩት የካራት፣ የወላይታ ሶዶ፣ የአርባ ምንጭና ጎፋ መናኸሪያዎች በቀጣይ መቶ ቀናት ለማጠናቀቅ በርብርብ እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ቢሮ ሀላፊው አስታውቀዋል።
እንደ ብርሀኑ (ዶ/ር) ገለጻ ለዲላ ከተማ መናኸሪያ 60 ሚሊዮን በጀት የተያዘ ሲሆን የጂንካው የደረቅ ጭነት መናኸሪያም በ33 ሚሊዮን ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛል።
መናኸሪያዎቹ የትራፊክ ፍሰትን ከማቀላጠፍ በተጨማሪ ለተሽከርካሪዎች ደህንነትና ለከተሞች መሰረተ ልማት ጥበቃ የጎላ ድርሻ እንደሚኖራቸውም አመልክተዋል።
በተያያዘ በክልሉ ከ68 በላይ የህዝብ መናኸሪያዎች እንዳሉ ያነሱት ብርሀኑ (ዶ/ር)፣ እነዚህ መናኸሪያዎች አስፈላጊ መሰረተ ልማት እና ቴክኖሎጂ የተሟላላቸው ባለመሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ችግሩን ለማቃለል በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ያሉ የህዝብ መናኸሪያዎችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚከናወንም አመልክተዋል።
በተለይ በህብረተሰብ ተሳትፎ በዲላ፣ ወላይታ ሶዶ እና አርባ ምንጭ ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ መናኸሪያዎችን ግንባታ ለማከናወን የቦታና የዲዛይን ርክክብ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
ዲላ ከተማ በርካታ የጭነት ተሽከርካሪዎች የሚያርፉበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዲላ ከተማ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ መምሪያ ሃላፊ አቶ አብነት ሽፈራው ናቸው።
በከተማዋ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች መናኸሪያ ባለመኖሩ አሽከርካሪዎች በመንገድ ዳር መኪና ለማቆም መገደዳቸውን ነው የተናገሩት።
ይህም ለመንገድ ዳር ትቦዎች መበላሸት፣ ለአስፓልት መንገድ መቦርቦር እና ለመሰረተ ልማት ውድመት ከማጋለጡ ባለፈ በትራፊክ ፍሰቱ ላይ ጫና ማሳደሩን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማው ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ያለው የደረቅ ጭነት መናኸሪያ ይህን ችግር ከመፍታት ባለፈ ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
በዲላ ከተማ አሽከርካሪው ወጣት ደረጀ ዓለሙ በበኩሉ ከባድ የጭነት መኪኖች ለረጅም ሰዓት በከተማው ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ መቆማቸው ለትራፊክ አደጋ መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግሯል።
ለጭነት ተሽከርካሪዎች የማሪፈያ ቦታ መዘጋጀቱ የትራፊክ ፍሰቱን እንደሚያቀላጥፍና የሚያገኙትን ገቢም ያሳድጋል የሚል ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።