ቀጥታ፡

በአፍሪካ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ሲወዳደሩ ሊተገበር የሚችል ግልፅ የኢኮኖሚ ፕሮግራም ማቅረብ አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ሲወዳደሩ ሊተገበር የሚችል ግልፅ የኢኮኖሚ ፕሮግራም ማቅረብ እንዳለባቸው የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ገለጹ።

2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄዱን ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ በጉባኤው ከመደመር ፍልስፍና የተቀዳውን የፖለቲካ ፓርቲ የለውጥ አስተዳደር ልምዷን አቅርባለች።

ከዚህም ባሻገር በአፍሪካ ምርጫ ከማሸነፍ ወደ ኢኮኖሚ ሽግግር በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፓናል ውይይት ተደርጓል።

የላይቤሪያ አንድነት ፓርቲ ሊቀ መንበር ሉተር ትራፕህ (ዶ/ር) የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ወረቀት ላይ ያለ ፕሮግራም መልካም መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን ትግበራ ላይ የተለየ መሆኑን ገልጸው፤ ይሄ አይነት አካሄድ መቆም አለበት ብለዋል።

ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የብልፅግና ፓርቲ የዜጎችን የኢኮኖሚ ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ አጀንዳ ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በግልፅ ማሳየቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፤ የምርጫ የመጨረሻ ግብ ሥልጣን መያዝ መሆን የለበትም ብለዋል።

የምርጫው ውጤት የዜጎችን ህይወት በመሰረታዊነት የሚያሻሽል የኢኮኖሚ ሽግግር የሚፈጥር መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በመደመር ፍልስፍና እየተመራች ግልጽ ፖሊሲና ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት መሰረታዊ ለውጥ አስመዝግባለች ብለዋል።

የጋና ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ኮንግረንስ ሊቀ መንበር ጆን አሴዱ ንኬቲህ ብልፅግና ፓርቲ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የሚመክሩበትን መድረክ በማዘጋጀቱ ምስጋና አቅርበዋል።

በአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት የምንገባውን ቃል ወደ መሬት ተግብረን ማሳየት ይኖርብናል ብለዋል።

የኢኮኖሚ ፕሮግራሞችን በማጥራት፣ ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በመለየት የሚተገበር ርዕዮት መቅረፅ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኮቲዲቯር አይቮሪያን ፖፑላር ፍሮንት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ፓስካል አፊ ጉይሳን፤ በምርጫ ያሸነፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገራቸውን ኢኮኖሚ ማሸጋገር አለባቸው ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ግልፅና የሀገራቱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የኢኮኖሚ ፕሮግራም ከሌላቸው በምርጫ መሳተፍ እንደማይገባቸው ገልጸዋል።

ፓርቲዎች በዜጎች ተጠቃሚነትና ዲሞክራሲ ግንባታ የህዝብን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ርዕዮት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

የቡሩንዲ የዲፌንስ ኦፍ ዲሞክራሲ ብሔራዊ ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ሪቨሪያን ንዲኩሪዮ አፍሪካውያን በትብብር የኢኮኖሚ ፖሊሲ መገንባት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ተዓማኒነት ያለው፣ የሚለካና ሊተገበር የሚችል የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም እንዲቀርጹም አሳስበዋል።

አፍሪካ የምኞት ሀይቅ ሆና መቀጠል የለባትም ያሉት ዋና ጸሀፊው፤ ዕቅዶች ከምኞት አልፈው ገቢራዊ መደረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም