ቀጥታ፡

የመደመር ፍልስፍና በትክክለኛው አቅጣጫ እየተተገበረ መሆኑን ባለፉት ስምንት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች ማሳያዎች ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር ፍልስፍና በትክክለኛው አቅጣጫ እየተተገበረ መሆኑን በኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተመዘገቡ ሁሉን አቀፍ ስኬቶች ማሳያዎች ናቸው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄዱን ቀጥሏል።


 

ኢትዮጵያ በጉባኤው ከመደመር ፍልስፍና የተቀዳውን የፖለቲካ ፓርቲ የለውጥ አስተዳደር ልምዷን አቅርባለች።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያን የለውጥ አስተዳደር ልምድ አጋርተዋል።

ኢትዮጵያ በመደመር ፍልስፍና በሚመራው የብልፅግና ፓርቲ ውጤታማ የለውጥ አስተዳደር ማንበር መቻሏን ገልጸዋል።

የመደመር ፍልስፍና የተቀናጀው በህዝብ መሰረትና በሚዛናዊነት ግንባታ ላይ መሆኑን ገልጸው፤ ነባራዊ ሁኔታን ከማህበረሰቡ ስሪት ጋር ያጣጣመ ነው ብለዋል።

መደመር መዳረሻው ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ ነው ያሉት አቶ አደም፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት ከተመዘገቡ ስኬቶች ጀርባ የመደመር ፍልስፍና እንደነበር ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት አካታች ሰነድ በማዘጋጀት ሁሉም ተቋማት ገቢራዊ እንዲያደርጉት ሆኗል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ተጨባጭ ለውጥ በማስመዝገብ ከሁለት ዓመት በፊት ራሷን መቻሏን በመግለፅ፤ የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።


 

መደመር ኢንዱስትሪውን በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አብዮት የሥራ ዕድል መፍጠርና የወጪ ንግድ ማሳደግ ችሏል ብለዋል።

በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን ክብር የሚመጥን ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ማስቻሉንም ገልጸዋል።

የመደመር ፍልስፍና በኮሪደር ልማት መርሃ ግብር የኢትዮጵያን ዘላቂ ክትመት በመምራት ገንቢ ሚና ተወጥቷል ብለዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ የአሕጉሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ስርዓት ለማንበር የመደመር ፍልስፍና መንገድ ጠቋሚ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም