ብዝሀነትን በአግባቡ ማስተናገድ ጠንካራ ሀገራዊ ስሜትና አንድነትን ለመገንባት የጎላ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
ብዝሀነትን በአግባቡ ማስተናገድ ጠንካራ ሀገራዊ ስሜትና አንድነትን ለመገንባት የጎላ ሚና አለው
አዳማ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ):-ብዝሀነትን በአግባቡ ማስተናገድ ጠንካራ ሀገራዊ ስሜት እና አንድነትን ለመገንባት የጎላ ሚና እንዳለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ ለትምህርት ተቋማት ያዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግስታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲ አንድነትና የሕገ መንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ወይዘሮ ባንችይርጋ መለሰ እንዳሉት፤ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "በብዝሃነት የደመቀች፣ በምክክር የጸናች፣ ሥልጡን ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል ይከበራል።
የቀኑ መከበር ብዝሀነትን ለሀገራዊ ዕድገት ለመጠቀም እንዲሁም ልዩነቶቻችንን በምክክርና በመግባባት ፈትተን ለጋራ ስኬት በአብሮነት እንድንቆም የሚያደርገን ነው ብለዋል።
"ብዝሀነትን ማስተዳደር ለጠንካራ የጋራ ዜግነትና ሀገራዊ አንድነት" በሚል ርዕስ ለትምህርት ተቋማት እየተሰጠ ያለው ስልጠና፤ ጠንካራ የዜግነት ስሜትንና ዘላቂ ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባት ሚናው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብዝሀ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶችና የተለያዩ አመለካከቶችን በማስተናገድ በእውቀት የበቃ ዜጋን ለማፍራት ወሳኝ አቅም እንዳላቸውም አስረድተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሕገ-መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፣ ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት ነው።
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር በሕብረተሰቡ ውስጥ የብዝሀነት እሴትን በማስረጽ ረገድ ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሀገሪቱ የእውቀት ምሶሶ እና ወጣቶች የሚቀረጹባቸው ማዕከላት መሆናቸውን ያወሱት ኃይለኢየሱስ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲዎች የብዝሀነትን ጠቀሜታ ከግቢያቸው ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ በማስረዳት በኩል ይበልጥ ሊሰሩ እንደሚገባ መክረዋል።
ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ ከሀገሪቱ የተውጣጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሕገ-መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል እንዲሁም የክልል ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።