በሲዳማ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ለእንስሳት ዝርያ ማሻሻልና ለወተት ሃብት ልማት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ለእንስሳት ዝርያ ማሻሻልና ለወተት ሃብት ልማት ትኩረት ተሰጥቷል
ሀዋሳ፣ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ለእንስሳት ዝርያ ማሻሻልና ለወተት ሃብት ልማት ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው የሩብ ዓመቱን የሌማት ትሩፋት ሥራዎች የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ የሚመክር መድረክ ዛሬ በሀዋሳ አካሂዷል።
የቢሮ ኃላፊው አቶ አሰፋ ፎና በወቅቱ እንደገለጹት፣ በክልሉ በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ለእንስሳት ዝርያ ማሻሻልና ለወተት ሀብት ልማት ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚህም በተያዘው ዓመት በክልሉ ከ350 ሺህ በላይ የዳልጋ ከብቶችን ዝርያ የማሻሻል ሥራ ለመሥራት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
ከዚህም 202 ሺህ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ጥጃዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፣ በዚህም በሩብ ዓመቱ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት እንደተቻለ ጠቁመዋል።
24 ነጥብ 2 ሚሊዮን እንቁላል ጣይ ዶሮዎችና 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት በበጀት ዓመቱ ለማሰራጨት ታቅዶ፣ በሩብ ዓመቱ ከተያዘው ዕቅድ አንጻር 85 በመቶውን ማከናወን እንደተቻለ ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ዳዊት ሀዬሶ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በክልሉ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
እነዚህን ውጤቶች አጠናክሮ ለማስቀጠል የእንስሳትን ዝርያ የማሻሻልና የወተትና ወተት ተዋጽኦ ምርቶችን የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።
መርሀ ግብሩ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር በዶሮ፣ በዓሳ፣ በወተት ላም እርባታና በንብ ማነብ ዘርፍ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁትን በማኅበር በማደራጀት የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርም አስረድተዋል።
የማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ በበኩላቸው፣ በዞኑ የዶሮ፣ የወተትና የንብ መንደሮችን በክላስተር በማደራጀት አርሶ አደሩና በማኅበር የተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገልጸዋል።
በዞኑ ከሚገኘው ይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር ትስስር በመፍጠር ወተትና ማር ለፓርኩ እየቀረበ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በመድረኩም የክልሉ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎችና ሴክተር አመራሮች ተገኝተዋል።