የመደመር መንግሥት ታላቁ ስትራቴጂ ሉዓላዊነቷ የተከበረና በአፍሪካ መሪ ሆና የምትቀጥል ኢትዮጵያን የበለጠ ለመገንባት ያለመ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት ታላቁ ስትራቴጂ ሉዓላዊነቷ የተከበረና በአፍሪካ መሪ ሆና የምትቀጥል ኢትዮጵያን የበለጠ ለመገንባት ያለመ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት ታላቁ ስትራቴጂ ሉዓላዊነቷን ፣ አንድነቷንና ጽናቷን የጠበቀች፣ አምራችና በአፍሪካ መሪ ሆና የምትቀጥል ኢትዮጵያን የበለጠ ለመገንባት ያለመ መሆኑን የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።
የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ዙሪያ የፌደራል መንግስት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በሚወጡ መመሪያዎችና የህግ ማዕቀፎች ላይ ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የመደመር ታላቁ ስትራቴጂ ሉዓላዊነቷን፣ አንድነቷንና ጽናቷን የጠበቀች፣ አምራች የሆነችና በአፍሪካ መሪ ሆና የምትቀጥል ኢትዮጵያን ለመገንባት ያለመ ነው።
የዚህ ስትራቴጂ ዋነኛ የስኬት መለኪያዎች መካከል ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻልና የዜጎችን እርካታ ማረጋገጥ ነው ብለዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙም እነዚህን ዓላማዎች እውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
በዚህም የመንግሥት አስተዳደርና አገልግሎት ማሻሻያ ፖሊሲ ተቀርጾ፣ ስትራቴጂዎች፣ መመሪያዎችና የሥራ ደረጃዎች ተዘጋጅተው ሪፎርሙን ተግባራዊ በማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዛሬው ውይይት የሚፈተሹት 18 መመሪያዎች የሪፎርሙን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተግባራዊ ለማድረግ እና ተቋማዊ አቅም ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው አብራርተዋል።
ዲጂታል አሠራርን ማስፋፋት የአገልግሎት ሂደቶችን ለማዘመን እና ተቋማት በተሻለ ብቃት ሕዝብን እንዲያገለግሉ ከሚያስችሉ የሪፎርሙ ዋና አቅጣጫዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
የተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች በጋራ የሪፎርሙ ባለቤት በመሆን መንቀሳቀስ ከቻሉ፣ ዘመናዊ አሠራርን የሚያሰፍኑና ዜጎች የሚረኩባቸውን ተቋማት በአጭር ጊዜ ውስጥ መገንባት እንደሚቻልም አስገንዝበዋል።
የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ውጤታማ ለማድረግ የሪፎርሙ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂዎች፣ ማኑዋሎችና የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
የሪፎርሙ ሰነዶች ከፌደራልና ከክልል ተቋማት ባለሙያዎች ጋር በትብብር መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፣ የሪፎርሙን ትግበራ ለማሳለጥ የተዘጋጁ ማኑዋሎች ለተቋማት እንዲደርሱ የሚሰራጩ መሆኑን ገልጸዋል።
የሪፎርሙን አፈጻጸም የሚመራ የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ረገድ አዋጁ መጽደቁን፣ ደንቦች መውጣታቸውንና መመሪያውም በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተቋማቱ የዜጎችን እርካታ ለማሳደግ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቶችን ማሻሻል፣ ዲጂታል አሠራርን ማስፋፋት፣ የሠራተኞችን ብቃት ማሳደግና የተቋማትን የአፈጻጸም ደረጃ በተከታታይ መገምገም እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአገልግሎት ጥራትንና የዜጎችን እርካታ ለማሳደግ ተቋማት የአገልግሎት ተምሳሌት ሆነው እንዲቋቋሙ መደረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታልና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት ተፈጥሮ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሠራተኞች ብቃት ምዘና ዓላማው የብቃት ክፍተቶችን በመለየት ለመንግሥት ተልዕኮ ብቁ የሆኑ ሠራተኞችን ማፍራት መሆኑን ገልጸው፣ ምዘናው በዲጂታል ሥርዓት ከሰው ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ እንዲከናወንና ሠራተኞች ውጤታቸውን ወዲያውኑ እንዲያውቁ መደረጉን አስረድተዋል።