ቀጥታ፡

የባህር በር - አዲስ ታሪክ የሚጻፍበት ብሔራዊ አጀንዳ! 

ሚዛን፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)---የባህር በር - አዲስ ታሪክ የሚጻፍበት ብሔራዊ አጀንዳ! 

በቀደሰ ተክሌ (ከሚዛን አማን ኢዜአ ቅርንጫፍ)

ምድረ ቀደምቷ ሀገር ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ብቻ ሳትሆን የስልጣኔ እልፍኝም ነች። የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ሀብቶቿን ለመቀራመት ዓለም ዓይኑን የጣለባት የምሥራቅ አፍሪካዋ ኮከብ ናት። በቅርብም ሆነ በሩቅ ታሪካዊ ጠላቶች ስላሏት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ታሪኳን ለማበላሸት የሚሠሩ ትናንትም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ። ከሀብቷ መጠቀም ያለባትን እንዳትጠቀም፣ ማደግ ባለባት መጠን እንዳትድግና ድሀ ሆና እንድትኖር ለማድረግ የሚታትሩ ብዙ ናቸው።

አቅሟን የማዳከም መንገድ ተደርጎ የተወሰደው አንዱ እንድትከፋፍል ማድርግ ሲሆን ሌላው የዓለም አቀፍ ሕግን ተከትላ የተፈጥሮ ሀብቶቿን እንዳትጠቀም በሴራ ሆን ተብሎ የማጠር ሥራ ተሠርቶባታል። በዚህም ያላትን የባሕር በርና ወደብ እንድታጣ ተደርጓል። ጫናው በእጅ አዙር የባርነት ቀንበር የመጫን ያህል የከበደ ቢሆንም ቅሉ በጠበቁት ልክ ሆኖ አልቀጠለም።

ሉዓላዊነቷን አጥታ እንድትፈርስ ሲታገሏት ዘመናት ቢነጉድም ኢትዮጵያ ጠንካራ ሕዝብና መንግሥት ስላለት ፈተናዎችን ከእግሮቿ በታች እያደረገች ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ዛሬም ድረስ እየኖረች ነው።

የአሁኑ ትውልድም ለኢትዮጵያ ክብር ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ የአባቶቹ ልጅ ሆኖ ስሟን በዓለም መድረክ ከፍ እያደረገ ይገኛል። ዛሬን መጠበቅ እና ነገን መገንባት ብቻ ሳይሆን ከትናንትናው የተበላሸውን ለይቶ ማረም ላይም ትኩረት አድርጓል። የዚሁ ተግባር አንዱ አካል ጠላት ያጠፋውን የባህር በር ባለቤትነት ታሪክ ማደስ ነው።

ትናንት በኢትዮጵያ ምድር የተደራጀ ቴክኖሎጂ የለም፤ የበለጸገ መሳሪያም የለም፤ በሳይንስ የመጠቀ የሰው ኃይልም በብዛት የሚቆጠር አልነበረም። ያም ሆኖ ኢትዮጵያን ጠላቶች መወንጀልና መተንኮስ እንጂ ማንበረከክ አልተቻላቸውም። በምትኩ የድል ጽዋን ከፍ ያደረጉት፣ የሉዓላዊነት አክሊል የተቀዳጁትና የነጻነት ዓርማን ያውለበለቡት ኢትዮጵያውን ናቸው። ዛሬ ታሪክ እንደዘመኑ ተቀይሯል። ኢትዮጵያ ንቁ ሕዝብ፣ ብቁ ኃይል፣ ምሉዕ ቴክኖሎጂና ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ሆናለች። ስለዚህ በዚህ አቅሟ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ትናንትንም ታክማለች። የወደብ ባለቤትነት ታሪካችን በልጆቿ የተባበረ ክንድ ተመልሶ ሌላኛውን ብሔራዊ ድል የሚሆንበት ወቅት ላይም ተቃርበናል።


 

 በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አጥናፉ ምትኩ እንደሚሉት አዱሊስ የሚባለው የኢትዮጵያ ወደብ በአክሱም ዘመን መንግስት እስከ 8ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ወደብ ነው። የውጭ ንግድና ሌሎችንም ተግባራት ለማሳለጥ ያገለግል እንደነበርም ያወሳሉ። ምጽዋ፣ አሰብ፣ ዘይላ የሚባሉ ወደቦችም ነበሩን። ይህ ኢትዮጵያ በባሕር በር አጠቃቀም ላይ ምን ያህል ገናና ታሪክ እንዳላት አመላካች የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው ሲሉ በማሳያነት ይጠቅሳሉ።

ይህን በሴራ ከእጃችን የወጣውን የወደብ ባለቤትነት ታሪክ ማስመለስ የዚህ ዘመን ትውልድ ኃላፊነት ሆኖ ተከስቷል። ለዘመናት አይነኬ አጀንዳ ተደርጎ ታፍኖ የቆየው የመብትና የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ ዛሬ ከተሸበበት ወደ ፊትለፊት ወጥቷል።

የጥያቄውን መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያውን ልብ ውስጥ ጥለው ሕዝቡ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያለማመንታት ተስማምቶበት ጥያቄውን እያስተጋባ ይገኛል። የተደበቀ ሕመም ሆኖ የቆየባቸው ዜጎች በእንባ ጭምር ስሜታቸውን ሲገልጹ ኢትዮጵያ ከአብራኳ ተመልክታለች።

አሁን ለኢትዮጵያውያን የባሕር በር ባለቤት የመሆን ጉዳይ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር አዲስ የጋራ ትርክት መገንቢያ ፕሮጀክት እንደሆነም መምህር አጥናፉ ይናገራሉ። ይህም ብቻ አይደለም የወደብ ባለቤትነት ጥያቄ የኢትዮጵያውያን ሌላኛው ዓድዋ ሆኖ አዲስ ታሪክ የሚጻፍበት ብሔራዊ አጀንዳ ነው።

የባሕር በር የተሰበረን የመጠገን፤ የተጣመመን የማቃናት አደራን ኢትዮጵያውያን የሚወጡበት የዜግነት ምልክትም ጭምር ነው። ይህን የትውልድ አደራ ለመወጣት መደማመጥና መሪን መከተል ቀዳሚ ተግባር ነው። ይህ ደግሞ በዘመን ጅረት የማይወይብ የኢትዮጵያውያን ደማቅ እሴት በመሆኑ ዛሬም እንደ ጥንቱ ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአንድነት ቆመዋል። ይሄም የጥያቄው መልስ ግማሽ ምዕራፍ ነው።

ኢትዮጵያ ያላት የሕዝብ ብዛት፣ ለቀይ ባሕር ያላት ቅርበት፣ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴና አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የባሕር በር በመሠረታዊነት እንደሚያስፈልጋት አመልካች ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው። ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ሆነች ማለት በለውጥ ሂደት ላይ ላለው ኢኮኖሚዋ መስፈንጠሪያ ሆኖ የሚያገልግል መሳርያ አገኘች ማለት ነው።

የወደብ ባለቤት መሆን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ረገድ ያለው ትርጉምም ሰፊ ነው። በየእለቱ ከኢትዮጵያ ኪስ ወጥቶ ለወደብ ኪራይ የሚወጣው ወጪ ሌላ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማት ለማከናወን ያስችላል። በወደብ ቀረጥ ምክንያት በምርቶች ላይ የሚጨመር የዋጋ ጭማሪ በትክክለኛ ሚዛን ሲቀመጥ ገበያን የማረጋጋት ተስፋው ትልቅ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ለቀጠናው ሰላምና የደህንነት ጉዳይ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል።

ይህን እውነት ለዓለም አቀፍ ሕዝብ በመግለጥ ዓለም የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በደንብ እንዲገነዘብ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው። ኢትዮጵያ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተፈጥሮ ሀብቱ ተጠቃሚ ለመሆን ያላትን መሻት የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ለማሳየት የምታደርገው እንቅስቃሴም በጉዳዩ ላይ እያደር በጎ ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚያስችል ነው።

ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት መመራት ከጀመረች ወዲህ በርካታ የዲፕሎማሲ ድሎችን እየተቀዳጀች መምጣቷ አሁን ላይ የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን መንገድ ቀና ያደርገዋል ያሉት ደግሞ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር መላኩ መሸሻ ናቸው።


 

አቅም መፍጠር አንዱ አስቻይ ሁኔታ መሆኑን ይጠቅሳሉ። የዲፕሎማሲ ጎዳናው መስተካከል ዓለም አቀፍ ድጋፍን በእጅ እንደማስገባት ነው። ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ጎብኝተው የሚመለሱ ኃያላን ሀገራት መሪዎች ለብሔራዊ ጥቅማችን መጠበቅ እንደ አንድ አቅም ሊታዩ ይችላሉ ሲሉም ይገልጻሉ። ይህ በፖለቲካው ዓለም ትልቅ ትርጉም ያለው ሲሆን ኢትዮጵያ በዘርፉ ስኬታማ መሆኗንም አንስተዋል።

ስለዚህ የባሕር በር ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል አያስፈልጋትም ከሚል እይታ ተሻግሮ በየትኛው አግባብ ማግኘት አለባት የሚለው ሁሉንም ሊያግባባ የሚችል ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ በውጭ ፖሊሲ ለዓለም ተሞክሮ የሚሆን ፖሊሲ አላት።

ለጎረቤት ቅድሚያ የሚሰጥና የሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ያተኮረም ነው። እነዚህ ወርቃማ ፖሊሲዎች ለቀጣናው ደህንነትና ዘላቂ ሰላም እንዲሁም የተዋጣ የልማት አቅም ለመፍጠር ሁነኛ እሳቤ ናቸው። እነዚህን እውነታዎች ታሳቢ ያደረገ የባሕር ባለቤትነት ጉዳይ በዲፕሎማሲ ታጅቦ እውን እንዲሆን የተጀመረው ጥረት እስከዳር መጠናከር አለበት።

ለዚህ ደግሞ ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ ሥርዓትን መከተል አስፈላጊ በመሆኑ ከመደበኛው የመንግሥት የዲፕሎማሲ ተግባር ባሻገር በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲጂታል ሚዲያን መሠረት ያደረገ የዲፕሎማሲ ተግባርን ማስፋት እንዳለባቸው መምህር መላኩ አመልክተዋል።

የወደብ ባለቤት ለመሆን የሚደረገው እንቅስቃሴ የአንድ ወቅት የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ አይደለም። እስከ መጨረሻው ተጉዞ ኢትዮጵያን ከፍ የማድረግና ዜጎቿን የማበልጸግ ራዕይ ያለው ጉዞ እንጂ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም