የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት ሀገራዊ አንድነትን ለሚያጎለብቱ የትርክት ግንባታ ሥራዎች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት ሀገራዊ አንድነትን ለሚያጎለብቱ የትርክት ግንባታ ሥራዎች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል
ቦንጋ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት የህዝቦችን አብሮነትና ሀገራዊ አንድነትን ለሚያጎለብቱ ብሔራዊ የትርክት ግንባታ ሥራዎች ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተገለጸ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ "ጠንካራ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ለክልላችን ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ ካሉ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት አመራሮች ጋር በቦንጋ ከተማ መክሯል።
በመድረኩ የተገኙት የክልል የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ እንደገለፁት፤ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የመንግሥት ፖሊሲዎችና ሕጎች ወደሕዝብ ደርሰው በተገቢው እንዲተገበሩ ሚናው የጎላ ነው፡፡
በተጨማሪም ሕዝብን በማነቃቃትና ተሳትፎውን በማጠናከር የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች እንዲሳኩ የማድረግ ትልቅ አቅም እንዳለው አንስተዋል።
በመሆኑም በክልሉ ያሉ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት ሀገራዊ አንድነትን ለማጎልበትና ብሔራዊ ትርክትን ለመገንባት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች በሕዝብ ዘንድ እንዲሰርፁ በማድረጉ በኩል ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በተለይ ጽንፍ የያዙና የተሳሳቱ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ እውነታውን ለህዝብ ማሳወቅ እንዳለባቸው አንስተዋል።
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት ባለፉት ዓመታት በክልሉ በሁሉም ዘርፎች ለተመዘገቡ ውጤቶች ትልቅ አበርክቶ እንደነበራቸው ያነሱት አቶ ነጋ ፣ በቀጣይም የክልሉ ማንሰራራት እውን እንዲሆን ጠንክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሀሲያ አሊ በበኩላቸው፤ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ መረጃን ከማስተላለፍ ባለፈ፣ በመንግስትና በሕዝብ መካከል ጤናማ ግንኙነት በመፍጠር የልማትና የሰላም ሥራዎችን ያሳልጣሉ ብለዋል።
ክልሉ በርካታ የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የባህልና የሰው ሀይል ሀብቶች እንዳሉት አስታውሰው፣ እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ ከማስተዋወቅ ባለፈ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ዘመኑ የሚፈልገውን እውቀትና ክህሎት በመላበስ ፈጠራን፣ ፍጥነትንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ ሀሰተኛ መረጃዎችን መታገልና እውነታውን ለህዝብ ማሳወቅ ይገባቸዋል ብለዋል።
በመድረኩ በክልሉ የሚገኙ ሚዲያዎች እና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መዋቅር የሥራ ሀላፊዎች ተሳትፈዋል።