በአፍሪካ ስልጣንን ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር መሞከር ለአለመረጋጋትና ግጭት የሚጋብዝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ስልጣንን ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር መሞከር ለአለመረጋጋትና ግጭት የሚጋብዝ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ስልጣንን ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር መሞከር ለአለመረጋጋትና ግጭት የሚጋብዝ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።
2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ እንደገለጹት፤ በአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህዝብና በተቋማት መካከል ድልድይ በመሆን ማገልገል አለባቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለአፍሪካ ለውጥ ለፈጠሩት የፖለቲካ ራዕይ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 የዲሞክራሲ አስተዳደር ስርዓት በአሕጉሪቱ የተቀናጀ የፖለቲካ ስርዓት መፍጠር እንዳለባቸው መደንገጉን ገልጸዋል።
በአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖሊሲ የተደገፈ የሕዝብ አገልግሎት መስጠት አለባቸው ያሉት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ከዚህም ባለፈ በህዝብና ተቋማት መካከል ድልድይ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
መሪ ፓርቲዎች ህገ መንግስታዊ አስተዳደር የመነጨ ተዓማኒ ምርጫ ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
በፓርቲዎች መካከል ውይይትና ንግግር ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ በአፍሪካ ስልጣንን ኢ- ሕገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር መሞከር ተገቢ አይደለም ብለዋል።
ይህም ለግጭትና አለመረጋጋት የሚጋብዝ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአፍሪካ ሕብረት ኢ -ሕገ መንግስታዊ አካሄዶችን በፅኑ እንደሚያወግዝ ገልጸዋል።