ኢትዮጵያ ዘላቂ ዕድገትን የሚያረጋግጡ አስደናቂ የልማት ስኬቶችን እያስመዘገበች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዘላቂ ዕድገትን የሚያረጋግጡ አስደናቂ የልማት ስኬቶችን እያስመዘገበች ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ዘላቂ ዕድገትን የሚያረጋግጡ አስደናቂ የልማት ስኬቶችን እያስመዘገበች መሆኑን የአፍሪካ አስተዳደር ማዕከል ሊቀ መንበር ቤኔዲክታ ላሲ ገለጹ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት "እድገትን መምራት፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሀንዲሶች" በሚል መሪ ሃሳብ ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ይፋዊ የመክፈቻ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የአፍሪካ አስተዳደር ማዕከል ሊቀ መንበር ቤኔዲክታ ላሲ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት፣ በኃይል፣ በኢንዱስትሪና በምርታማ ሥራዎች ላይ ኢንቨስት አድርጋለች።
የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገቷም በየጊዜው ለውጥ እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሊቀ መንበሯ ጉባኤው በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄዱ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በዓድዋ ነፃነቷን በማስጠበቅ ለአፍሪካ የራስን ዕጣ ፈንታ የመወሰን መብት ዘላቂ ምሳሌ እንደሆነች ተናግረዋል።
ፓርቲዎች ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ለመንግሥት ሥራ መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ምርጫ አንድ ፓርቲን በአንድ ጀምበር ሥልጣን ላይ ሊያስቀምጠው እንደሚችል ጠቅሰው፤ ሀገር ለመምራትና ኢኮኖሚን ለማስተዳደር የሚያስፈልገው ዕውቀት ግን በአንድ ጀምበር እንደማይገኝ ተናግረዋል።
የፓርቲ ትምህርት ቤቶች፣ ኢንስቲትዩቶችና የምርምር መዋቅሮች ፓርቲዎች ሐሳቦቻቸውን እንዲፈትሹና ሰዎችን እንዲያዘጋጁ ጊዜ እንደሚሰጧቸው ገልጸዋል።
አፍሪካ ከፍተኛ የልማት ፋይናንስ ክፍተት እንዳለባት የገለጹት ሊቀ መንበሯ፤ በአህጉሪቷ ውስጥ ግን በቂ ሀብት እንዳለ አመልክተዋል።
ፓርቲዎች፣ የአስተዳደር ተቋማትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
አጀንዳ 2063 እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት በብዙ ሀገራዊ ምርጫዎች ውስጥ እንደሚያልፉ በመግለጽ፤ ፓርቲዎች ስምምነቶቹን ቢረዱ ውሳኔዎቹ መንግሥት ቢቀየርም እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ፓርቲዎች የሴቶችንና የወጣቶችን አስተዋጽኦ እንዲቀበሉም ጠይቀዋል።
ሊቀ መንበሯ ጉባኤውን ላስተናገዱት የኢትዮጵያ መንግሥትና ብልፅግና ፓርቲ ምስጋና አቅርበዋል።