የክልሉን የተፈጥሮ ጸጋ መሰረት በማድረግ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን የተፈጥሮ ጸጋ መሰረት በማድረግ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል
ቦንጋ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ያለውን የተፈጥሮ ጸጋ መሰረት በማድረግ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የክልሉ ልዩ ትኩረት መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር ፍቅሬ አማን ገለጹ።
የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ "ክህሎት መር ሥራ ዕድል ፈጠራ ለክልላችን ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ክልሉ በርካታ የተፈጥሮ ጸጋዎች እንዳሉት ገልጸው፣ ጸጋዎቹን በመጠቀም ወጣቱ የሥራ ልድል ተጠቃሚ እንዲሆንና ሀብት እንዲያፈራ መስራት ይገባል ብለዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራና ሠራተኛን ከማገናኘት ባለፈ ጤናማ አካባቢን የመፍጠር እና ሁሉንአቀፍ ብልፅግናን የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑንም አመልክተዋል።
በመሆኑም የሥራ ዕድል ፈጠራን ክህሎት መር በማድረግ ቀጣይነት ባለው መልኩ መስራት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የወጣቶችን ፍላጎት ለይቶ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባም አንስተዋል።
በዚህ ረገድ በክልሉ ባለፉት ጊዜያት በተሰሩ ሥራዎች በርካታ ወጣቶችን የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
ተደራጅተው ወደሥራ ለገቡ ወጣቶች ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት አቶ ፍቅሬ፣ የበለጸገችና ለዜጎች ምቹ የሆነች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
ቁጠባቸውን ማጠናከር፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎችን በማመቻቸት እና በቂ ድጋፍና ክትትል በማድረግ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማጎልበት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ በበኩላቸው፣ ክህሎት መር የሥራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከሥራ ፈላጊዎች ልየታ ጀምሮ በጥንቃቄና በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
ለወጣቱ ክህሎት መር ስልጠና ለመስጠት፣ የአካባቢን ጸጋ መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማጠናከር እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጭ ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘት እንደሚሰራም አመልክተዋል።
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ በበጀት ዓመቱ በክልሉ ለ151 ሺህ 708 ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል።
በዚህ ረገድ ባለፉት ሦስት ወራት በተደረገ እንቅስቃሴም በግብርና፣ በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ከ15ሺህ 170 በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በዘንድሮ የሥራ ዕድል ፈጠራ 330 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ፋንታሁን፣ 6ሺህ 343 ሄክታር መሬትም ለኢንተርፕራይዞች ለማስተላለፉ እንደሚሰራ አመለክተዋል።